በየዓመቱ ከ900 ሚሊዮን ቶን በላይ ምግብ ይባክናል

የተጣለ ምግብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ900 ሚሊዮን ቶን በላይ ምግብ እንደሚጣል አንድ ዓለም አቀፍ ሪፖርት አመላከተ።

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ የምግብ ብክነት አሃዝ እንዳመለከተው ለተጠቃሚዎች ከሚቀርበው ምግብ ውስጥ 17 በመቶ የሚሆነው በቀጥታ ወደ ቆሻሻ መጣያ ይገባል።

የምግብ ብክነቶቹ የሚያጋጥሙት በምግብ ቤቶች፣ በመገበያያ ስፍራዎች እና በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነው።

ለብክነት ከሚዳረገው ጠቅላላ የምግብ መጠን 60 በመቶ ያህሉ የሚውጣው ከመኖሪያ ቤቶች ነው ተብሏል።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የምግብ ብክነትን በመቀነስ ቢያንስ በእንግሊዝ ውስጥ አስገራሚ ውጤትን ማሳየቱ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት አጋር ድርጅት የሆነው 'ራፕ' የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት ሰዎች የሚገዙትን እና የሚመገቡትን ለመመጠን የበለጠ በጥንቃቄ ማቀድ ጀምረዋል ብሏል።

'23 ሚሊዮን የጭነት መኪናዎች ምግብ'

ሪፖርቱ "ከታሰበው እጅግ በጣም የሚልቅ" ዓለም አቀፋዊ ችግርን ጎላ አድርጎ አሳይቷል ሲሉ የራፕ ባልደረባ የሆኑት ሪቻርድ ስዋንኔል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በየዓመቱ የሚባክነው 923 ሚሊዮን ቶን ምግብ 40 ቶን የሚጭኑ 23 ሚሊዮን መኪናዎችን ይሞላል። ይህም ምድርን ሰባት ጊዜ ለማክበብ በቂ ነው" ብለዋል።

ሸማቾች ለምግብነት ከሚያውሉት የምግብ መጠን በላይ ስለሚገዙ ቀደም ይህ ሁኔታ የሀብታም አገራት ብቸኛ ችግር ተደርጎ ቢወሰድም የምግብ ብክነት ሁሉም ዘንድ የሚታይ ሆኗል።

በዝቅተኛ እና ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የችግሩ ስፋት እንዴት እንደሚለያይ ሪፖርቱ ጠቁሟል።

"ጉዳዩን ጠለቅ ብለን አልተመለከትንም። ነገር ግን ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የኃይል አቅርቦት እጥረት በመኖሩ ምክንያት አቀዝቅዞ የማቆየት ሰንሰለት ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ አይደለም" ብለዋል የዩኔፕ ባልደረባው ማርቲና ኦቶ።

እንደ ኦቶ ከሆነ አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ምግቦችን የማባከኑ መጠን አነስተኛ ነው።

እንደ ዩኔፕ ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ከሆነ በዚህ ዓመት መጨረሻ ከሚደረጉት ከዓለም የአየር ንብረት እና ብዝሃ ሕይወት ጉባኤዎች በፊት አገራት በጎርጎሮሳዊያኑ 2030 አገራት ቆሻሻን በግማሽ ለመቀነስ ቃል እንዲገቡ ግፊት እያደረጉ ነው።

"የአየር ንብረት ለውጥን፣ የተፈጥሮን እና የብዝሀ ሕይወት መጥፋትን እንዲሁም ብክነትን ለመቀነስ ከፈለግን በዓለም ዙሪያ ያሉ የንግድ ተቋማት፣ መንግሥታትና ዜጎች የምግብ ብክነትን በመቀነስ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው" ብለዋል።

የእንቅስቃሴ ገደብ ውጤት

የኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ ገደብ የምግብ ብክነትን እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል አስገራሚ ውጤት ያስገኘ ይመስላል።

የራፕ ጥናት እንዳመለከተው በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት ዕቅድ ማውጣት፣ በጥንቃቄ ማከማቸት እና በቡድን ማብሰል ከ2019 ጋር ሲነፃፀር የሰዎችን የምግብ ብክነት መጠንን በ22 በመቶ ቀንሷል።

"በቤታችን ተወስነን መቆየትን በቡድን ማብሰልን እና የምግብ ዕቅድን የመሳሰሉ ባህሪዎች እንዲጨምሩ አድርጓል። ከእንቅስቃሴ ገደቡ ስንወጣ ግን የምግብ ብክነትን እንደገና ሊጨምር ይችላል" ብሏል ሪፖርቱ።