የኮሮናቫይረስ ክትባት የተከተቡ የአፍሪካ መሪዎች የትኞቹ ናቸው?

ታትሟል

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪም በነገው ዕለት በአገራቸው ክትባቱን በይፋ መሰጠት መጀመሩን ለማስተዋወቅ ክትባቱን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የናይጄሪያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ልማት ዳይሬክተር ዶ/ር ፈይሰል ሹያብ ፕሬዝዳንቱ በቀጥታ በቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ለመከተብ የወሰኑት ናይጄሪያውያን እንዲከተቡ ለማበረታታት ነው ብለዋል።

የጋናው ናና አኩፎ አዶ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የኮሮናቫይረስ ክትባት ከወሰዱ የአፍሪካ ፕሬዝዳንቶች መካከል አንዱ ናቸው።

መሪዎች በሕዝብ ፊት ክትባቱን ሲወስዱ መታየታቸው ኮሮናቫይረስን በመዋጋት ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና ከማሳየቱ ባሻገር በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለክትባቱ በራስ መተማመን ይጨምራል ተብሎ ይታመናል።

በርግጥ የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ክትባትን ለማምረት ምንም ዓይነት አቋራጭ መንገድ አልተኬደም በማለት በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ በአንዳንድ ኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ግን ክትባቱ በችኮላ ተመርቷል ስለዚህም ውጤታማ አይደለም የሚል ጥርጣሬ ይታያል።

አኩፎ አዶ ራሳቸውም ቢሆኑ አንዳንድ የአገራቸው ዜጎች ክትባቱ የሰዎችን ዲኤንኤ ይቀይራል በሚል የሚነዙትን ወሬ "የማይረባ" ሲሉ አጣጥለውታል።

አንዳንድ ጋናውያን ደግሞ ክትባቱ የተሰራው አፍሪካውያንንን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ነው ብለው ያምናሉ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የርዕሰ ብሔርነት ቃለ መሃላ ከመፈፀማቸው በፊት አስቀድመው በቴሌቪዥን በቀጥታ ለህዝብ በሚተላለፍ ዝግጅት ላይ ተገኝተው የኮሮና ተህዋሲ መከላከያ ክትባት የወሰዱ ሲሆን "ምንም መጨነቅ አያስፈልግም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ወዲያው ደግሞ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን ክትባቱን ወስደዋል።

የአፍሪካ መሪዎችም በቴሌቪዥን በቀጥታ እየተላለከፈ ክትባቱን መውሰድ ጀምረዋል።

እስካሁን ድረስ የትኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ክትባቱን ወሰዱ?

ሲሼልስ

ፕሬዝዳነት ዋቭል ራምካላዋን የኮሮናቫይረስን መከላከያ ክትባት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ሲወስዱ የመጀመሪያው የአፍሪካ መሪ ናቸው።

የሲሼልሱ ፕሬዝዳንት የወሰዱት ክትባት ቻይና ሰራሹን ሲኖፋርም ሲሆን፣ አገራቸው በይፋ ክትባቱን መስጠት መጀመሯንም በዚያው አብስረዋል።

ደቡብ አፍሪካ

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ በአገራቸው ምንዱባን በሚኖሩበት አካባቢ ካሃዬሊትሻ በሚሰኝ የሕዝብ ሆስፒታል ተገኝተው በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ክትባቱን ወስደዋል።

ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት በማለት ዜጎቻቸው ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ያመረተውን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት በመንግሥት የጤና ተቋም ተገኝተው ቢወስዱ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለው አሳይተዋል።

ራማፎሳ በኋላ ላይም በትዊተር ገጻቸው ላይ ብቅ ብለው ሂደቱን "ፈጣን፣ ቀላል እና አንዳች ህመም የሌለው" ሲሉ ገልጸውታል።

ዚምባብዌ

የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ራሳቸው ክትባቱን ከመውሰድ ይልቅ ምክትላቸውን ወክለዋል። ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ የአገሪቷን የመጀመሪያ የኮቪድ-19 ክትባት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እየታዩ ወስደዋል።

ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ ስለምን ምክትላቸው ይህንን ወሳኝ ኃላፊነት ምክትላቸው እንዲወጡ ለምን እንደወከሉ አልታወቀም።

በርግጥ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴርም በመሆናቸውሊጭምር ሊሆን እንደሚችል ግምት አሳድሯል።

ሴኔጋል

የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የቻይናውን ክትባት ሲኖፋርም በቤተመንግሥታቸው ወስደዋል።

በእርግጥ ፕሬዝዳንቱ ይህንን ክትባት ሲወስዱ የመጀመሪያው አይደሉም።

ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ አገሪቱ በይፋ ክትባቱን መስጠት ስትጀምር 4000 ያህል ሴኔጋላውያን ፕሬዝዳንታቸውን ቀድመው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቱን ወስደዋል።

ሞሮኮ

ንጉሥ ሞሐመድ ስድስተኛ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትን በቤተመንግሥታቸው በመውሰድ የክትባቱን መጀመር ለአገራቸው ሕዝብ ይፋ አድርገዋል።

የአገሪቷ የጤና ሚኒስቴር እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች፣ የጤና፣ የደኅንነት እና የትምህርት ዘርፍ ሠራተኞች ክትባቱን እንደሚወስዱ ግልጽ አድርጓል።