ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሚያንማር ለተቃውሞ የወጡ ቢያንስ 18 ሰዎች በፖሊስ ተገድለዋል ተባለ
ትናንት በሚያንማር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ለመቃወም አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ፖሊስ ተኩስ ከፍቶ ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።
ይህ የሟቾች ቁጥር የአገሪቱ ዜጎች መፈንቅለ መንግሥቱን ለመቃወም ሰልፍ ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።
ሰልፈኞቹ የተገደሉት በዋና ከተማዋ ያንጎን ጨምሮ ዳዋይ እና ማንዳሌይ ሲሆን፤ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጪስ ተጠቅሟል። ጥይትም በብዛት ሲተኩስ እንደነበር ተገልጿል።
የጸጥታ ኃይሎች ለሳምንታት መቆጣጠር አቅቷቸው የቆየውን ተቃውሞ ለመበተን ማንኛውም አይነት ኃይል ለመጠቀም ዝግጁ ነበሩም ተብሏል።
የአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት አከናውነው ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ የኖቤል ተሸላሚዋ ኦንግ ሳን ሱ ቺ ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ መሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ይህ በእንዲ እንዳለ ሳን ሱ ቺ በጦሩ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጠበቆች ጋር መገናኘታቸው ተነግሯል።
ሳን ሱ ቺ ባለፉት 28 ቀናት ስፍራ ባልተገለጸ ቦታ በቁጥጥር ሥር ውለው ይገኛሉ። በኢንተርኔት ቪዲዮ አማካኝነት ፍርድ ቤት ዛሬ ቀረቡት ሳን ሱ ቺ፤ "በጥሩ ጤንነት ላይ" ይገኛሉ የተባለ ሲሆን፤ ጠበቆቻቸውን ማግኘት እንደሚሹ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።
እሁድ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ ምስሎች ላይ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከፖሊስ ለማምለጥ ሲሮጡ ታይቷል። ፖሊስም ሰልፈኞችን ለመቆጣጠር መንገዶችን ሲዘጋ የነበረ ሲሆን በደም የተሸፈኑ ዜጎች በጎዳናዎችም ታይተዋል።
የአሜሪካ የደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኃይል ተቃዋሚዎችን ለመቆጣጠር የሚደረገው እርምጃ ለማስቆም ተጨማሪ እርምጃዎች ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
''በቀጠናው ካሉ አገራትና ሌሎች በመላው ዓለም ከሚገኙ ወዳጅ አገራት ጋር በመሆን በዚህ ውሳኔ ውስጥ የተሳተፉትን በሙሉ ተጠያቂ ለማድረግ እንሰራለን'' ብለዋል ባወጡት መግለጫ።
አሜሪካ ከጅምሩ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን በመጣው ወታደራዊ መንግሥት ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው።
ቢቢሲ በቦታው ላይ ተገኝቶ መመልከት እንደቻለው በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ፖሊስም ቢሆን ሰልፈኞቹን ለመበተን የተቻለውን ነገር ሁሉ ሲያደርግ ነበር። ነገር ግን ተቃዋሚ ሰልፈኞች እራሳቸውን ከፖሊስ ለመከላከል ምሽጎችን እየሰሩ ሲጠባበቁ ነበር።
ምንም እንኳን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በጥይት ተመትተው ቢወድቁም ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ግን እስከመጨረሻው ድረስ ሳያፈገፍጉ ከፖሊስ ጋር ሲፋጠጡ ነበር ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት በተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ላይ የተወሰደውን እርምጃ የተቃወመ ሲሆን ከታማኝ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ ቢያንስ 18 ሰዎች እሑድ ዕለት ብቻ በፖሊስ ተገድለዋል ብሏል። ተጨማሪ 30 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
''የሚያንማር ዜጎች ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተቃውሟቸውን የመግለጽና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን የመጠቀም መብት አላቸው'' ብለዋል የሰብዓዊ መብት ቢሮው ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ።
በሚያንማር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በፈነዳው ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞን በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር እስካሁን በግልጽ አይታወቅም። ነገር ግን አንዳንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ድርጅቶች ቁጥሩ እስከ 850 ሊደርስ እንደሚችል ይገልጻሉ። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ብቻ ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።