ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክ የሚየንማር መንፈቅለ-መንግሥት መሪዎችን ከገፁ አገደ
ግዙፉ ማሕበራዊ ድር-አምባ ፌስቡክ የሚየንማር ወታደራዊ መሪዎችንና አጋሮቻቸውን ከገፁ አግዷል።
ኩባንያው እንዳለው ውሳኔውን የወሰደው "የሚየንማር ወታደራዊ መሪዎች ፌስቡክና ኢንስታግራም እንዲጠቀሙ ማድረግ ያለውን አደጋ ካጤነ' በኋላ ነው።
የሃገሪቱ ወታደራዊ ኃይል የ2020 ምርጫ የተጭበረበረ ነው ለማለት ፌስቡክን እንደ አንድ መድረክ ተጠቅሞ ነበር።
ከሚየንማር 54 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላዩ ፌስቡክ ይጠቀማሉ።
ለአንዳንዶች ፌስቡክ ማለት በይነ-መረብ ማለት ነው።
ኩባንያው ከቀናት በፊት የሃገሪቱን ወታደራዊ ኃይል ገፅ የፌስቡክን አጠቃቀም ሕግ ጥሷል በማለት ማገዱ ይታወሳል።
ወታደራዊው ኃይል በመንፈቅለ-መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ተቃዋሚዎችን አሥሯል፤ የኢንተርኔት አገልግሎት አቋርጧል፤ እንዲሁም ማሕበራዊ ድር አምባዎች እንዲዘጉ አዟል።
ፌስቡክ ረቡዕ አመሻሹን ባወጣው መግለጫ በፈረንጆቹ የካቲት 1 ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ወታደራዊ መሪዎቹን ማገድ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።
መፈንቅለ-መንግሥቱን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ቢያንስ ሶስት ሰልፈኞችና አንድ ፖሊስ ተገድለዋል።
ወታደራዊው መንግሥት ምርጫ በማሸነፍ ሥልጣን የያዙ ግለሰቦችን አሥሯል።
ፌስቡክ ጨምሮ ከሚየንማር ወታደራዊ ኃይል ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ ተቋማት በገፁ ማስታወቂያ እንዳያስኬዱ እንደሚያግድ አስታውቋል።
ግዙፉ ፌስቡክ እንዳለው እገዳው እንደ ጤና እና ትምህርት ሚኒስቴር ያሉ ሕዝብ አገልጋይ መሥሪያ ቤቶችን የሚመለከት አይደለም።
ወታደራዊው ኃይል ተቃውሞችን ለማርገብ በሚል ፌስቡክን ለተወሰነ ጊዙ ያክል አግዶ ነበር።
ሚየንማር ውስጥ በፌስቡክ አማካይነት ሃሰተኛ ዜናዎች ብዙ ጊዜ ይሰራጫሉ። በርካታ የመብት ተሟጋቾችም ይህን ሲተቹ ቆይተዋል።
መፈንቅለ-መንግሥቱ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ በፌስቡክ አማካኝነት የቡድሃ እምነት በሚበዛባት ሃገር የኃይማኖት ግጭት እንዳይነሳ ይፈራ ነበር።
በፈረንጆቹ 2014 ፀረ-ሙስሊም የሆኑት መነኩሴ አሺን ዊራቱ አንዲት የቡድሃ እምነት ተከታይ ታዳጊ በሙስሊም ወንዶች ተደፍራለች ብለው መልዕክት አጋርተው ነበር።
ከቀናት በኋላ በዚህ ዜና ምክንያት በተነሳ ግጭት ሁለት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
ከግድያው በኋላ መረጃውን ያጣራው ፖሊስ መነኩሴው ያሰራጩት መረጃ ሙሉ በሙሉ ሃሰተኛ እንደሆነ ደርሶበታል።
በ2017 ደግሞ በሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ በተነሳው ጥቃት ወቅት የፌስቡክ ስም በክፉ ሲነሳ ነበር።
አሁን የወታደሩ መሪ የሆኑት ሚን ኦንግ ሂያንግ በወቅት የሮሂንጃ ሙስሊሞች ከባንግላዴሽ የመጡ ናቸው ማለታቸው ይታወሳል።
ምንም እንኳ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ለዘመናት በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ሚየንማር ቢኖሩም በወቅቱ በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት ወደ በርካቶች ወደ ባንግላዴሽ ሸሽተው ነበር።
ፌስቡክ አሁን የወታደራዊ ኃይሉን መሪ ሚን ኦንግን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከገፁ አግዷል።
ፌስቡክ የአንድ ሃገር ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ባለሥልጣን ሲያግድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ፌስቡክ ሃሰተኛ መረጃዎች በገፁ ላይ ሲንሰራፉ አፀፋዊ ምላሽ አይሰጥም ተብሎ ብዙ ጊዜ ይተቻል።