በኢኳዶር እስር ቤቶች በተቀሰቀሰ ግጭት 75 እስረኞች ተገደሉ

ታትሟል

በኢኳዶር ሦስት እስር ቤቶች ውስጥ በተከታታይ በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ 75 እስረኞች መገደላቸው ተነገረ።

ማክሰኞ ዕለት በእስረኞች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለመቆጣጠር የአገሪቱ ጦር ሠራዊትና የአድማ ብተና ፖሊስ በእስር ቤቶቹ ውስጥ መሰማራቱ ተገልጿል።

ለዚህ በእስረኞች መካከል ለተከሰተው ግጭት ምክንያቱ በእስር በቤቶቹ ውስጥ ያሉ የወሮበላ ቡድኖችን ይመራ የነበረው ግለሰብ ባለፈው ታኅሣስ ወር ከተገደለ በኋላ የመሪነት ቦታውን ለመያዝ በተደረገ ፉክክር እንደሆነ ተገልጿል።

የኢኳዶር ወህኒ ቤቶች ኃላፊ እንዳሉት ግጭቱ የተነሳባቸው ሦስቱ እስር ቤቶች በአገሪቱ ካሉ 70 በመቶው እስረኞች የሚገኙባቸው ናቸው።

ኃላፊው ኤድሙንዶ ሞንካያ እንዳሉት በሦስቱ እስር ቤቶች ውስጥ በተከሰተው ግጭት 75 ሲሆን በየእስር ቤቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር የተለያየ ነው።

ከክስተቱ ጋር ተያይዞ በርካታ የፖሊስ መኮንኖች የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሁሉም የሞቱት ግን እስረኞች ናቸው።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ከግጭቱ በኋላ እንደተናገሩት የአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች በእስር ቤቶቹ የተከሰተውን ችግር በቁጥጥር ስር በማዋል ሕግ ማስከበራቸውን ገልጸዋል።

የእስር ቤቱ ኃላፊ እንዳስታወሱት ባለፈው ታኅሣስ ወር የወሮበሎቹ ቡድን መሪ የሆነው ጆርጌ ልዊስ ዛምብራኖ ከተገደለ በኋላ ውጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።

ኮኖሮስ የተባለው የወሮበላ ቡድን መሪ የነበረው ዛምብራኖ ከእስር ከተለቀቀ ከወራት በኋላ በአንድ ካፍቴሪያ ውስጥ ነበር የተገደለው።

ዛምብራኖ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ቡድኑ ከፍትኛ ገቢን የሚያስገኝ በአብዛኛው በእስር ቤት ውስጥና በውጪ በዕጽ ዝውውርና ሌሎች ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ የተሰማራ ነው።

የኢኳዶር የአገር ውስጥ ሚኒስትር በእስር ቤቶቹ ውስጥ ስለተከሰተው ግጭት እንደተናገሩት ምክንያቱ የወንጀለኛ ቡድኑን መሪነት ለመያዝ በተደረገ ትግል ምክንያት እንደሆነ ጠቁመው በእቅድና በተደራጀ ሁኔታ የተካሄደ እንደነበር ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥት ሁለት ጊዜ በአገሪቱ እስር ቤቶች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያው በአንድ ሳምንት ውስጥ 10 እስረኞች ከተገደሉ በኋላ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አንድ የሙስና ወንጀል ምስክር በእስር ቤቱ ውስጥ በመገደሉ ነው።