ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናው ፍርድ ቤት ባል ለቀድሞ ሚስቱ የጉልበት ካሳ እንዲከፍል ወሰነ
በቻይናዋ ዋና ከተማ ቤጂንግ የሚገኝ የፍቺ ክርክር ችሎት ሚስት በትዳር በቆዩባቸው ዓመታት ለሰራችው የቤት ውስጥ ሥራ ባል ካሳ እንዲከፍላት ውሳኔ ሰጠ።
ውሳኔው በቻይና በቅርቡ የፀደቀውን የፍትሃብሔር ሕግን ተከትሎ የተሰጠ ሲሆን ክፍያው ለቤት ሰራተኞች ከሚከፈለው ዋጋ ጋር ተነፃፅሮ በቻይና ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሰፊ ክርክር አስነስቷል።
የፍርድ ቤቱ መዝገብ እንደሚያስረዳው ቼን የተሰኘው ቻይናዊ ባል ባለፈው ዓመት ነበር ለችሎቱ የፍቺ ማመልከቻውን ያስገባው። ሚስት ዋንግ በበኩሏ ለፍቺው ፍላጎት ሳታሳይ ቆይታ ቼን የቤት ውስጥ ሥራ እንደማይሰራ እና ልጃቸውንም እንደማይንከባከብ ጠቅሳ የገንዘብ ካሳ ጠይቃለች።
በቤጂንግ የፋንግሻን ቀጠና ፍርድ ቤትም ለሚስት የፈረደ ሲሆን ባል በየወሩ ሁለት ሺህ ዩአን ቀለብ እንዲቆርጥ ወስኗል። ሚስት በአምስት ዓመት የትዳር ቆይታ ወቅት ላበረከተችው የቤት ውስጥ ሥራ ደግሞ 50 ሺህ ዩአን ይከፈላት ብሏል።
ከትላንት በስቲያ ሰኞ ችሎቱን ያስቻሉት ዳኛ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ጥንዶች ሲለያዩ የሚደረግ የንብረት ክፍፍል በተለይም ቁሳዊ የሃብት ክፍፍል ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል። ‹‹ነገር ግን የቤት ውስጥ ሥራ የማይታይ ሃብትን ይፈጥራል›› ሲሉ ዳኛው ገልፀዋል።
በያዝነው ዓመት የፀደቀው የቻይና አዲሱ የፍትሃ ብሔር ሕግ ጥንዶች በፍቺ ወቅት ልጆችን በማሳደግ፣ አዛውንት ቤተሰቦቻቸውን በመንከባከብ ወይም ወላጆቻቸውን በመርዳት ላይ አንዱ የበዛ ጫና ከነበረበት በፍቺ ወቅት ካሳ መጠይቅ እንደሚችል ይደነግጋል።
ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ጥያቄ ማንሳት የሚቻለው በጋብቻ ወቅት ቀድመው ከተስማሙ ብቻ ሲሆን ይህም በቻይና ያልተለመደ ድርጊት ነው።
ታዲያ በቻይና ሞቅ ያለ ክርክር ያስነሳው ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔን የሚመለከተው ሃሽታግ 570 ሚሊዮን ግዜ የታየ ሆኖ ተመዝገቧል።
አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች 50 ሺህ ዩአን ለአምስት ዓመት የቤት ውስጥ ሥራ በጣም ያነሰ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ‹‹በቤጂንግ አንድ የቤት ሰራተኛ ለአንድ ዓመት ያህል እንኳን ለመቅጠር ይህ ገንዘብ አይበቃም። ውሳኔው ቃላት እስከሚያጥሩኝ አስገርሞኛል፣ ይህ የቤት አመቤትነትን አሳንሶ ማየት ነው›› ሲሉ አንድ አስተያየት ሰጪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ወንዶች ቀድሞውንም የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሃላፊነት መጋራት አለባቸው ሲሉ ሌሎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በተጨማሪም ሴቶች ከጋብቻ በኋላ የሥራ ህይወታቸውን እርግፍ አድርገው መተው እንደሌለባቸው ሌሎች ሃሳባቸውን ሲገልፁ ተደምጠዋል።
‹‹ሴቶች ሁሌም ራሳችሁን ችላችሁ ቁሙ። ሥራችሁን ከጋብቻ በኋላ አትተዉ፤ ለራሳችሁ የራሳችሁ ማምለጫ መንገድ ይኑራችሁ›› የሚለው በማህበራዊ ሚዲያ በጉዳዩ ላይ ከተጋሩ አስተያየቶች አንዱ ነው።
አንድ የኢኮኖሚ እና ልማት ትብብር የተሰኘ ተቋም እንዳጠናው ቻይናዊያን ሴቶች በቀን አራት ሰዓት ገደማ ያለክፍያ ሥራ ላይ ያጠፋሉ፤ ይህም ከወንዶች 2.5 እጥፍ ይበልጣል።