ፌስቡክ በአውስትራሊያ የዜና ገጾች ላይ የጣለውን እገዳ አነሳ

ታትሟል

ፌስቡክ የአውስትራሊያ ተጠቃሚዎቹ ዜና እንዳያዩ ጥሎት የነበረውን እገዳ አነሳ።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ካሳለፍነው ሐሙስ ጀምሮ የአውስትራሊያ ተጠቃሚዎቹ በገጹ ላይ የሚሰራጩ የዜና ገጾችን እንዳያዩና እንዳያጋሩ አግዶ ነበር።

ኩባንያው ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው አውስትራሊያ ፌስቡክና ጉግል ለዜና ተቋማት ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ሕግ ማርቀቋን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ነበር።

የአውስትራሊያ የገንዘብ ሚኒስተር ጆሽ ፍርይንደርበርግ፤ ከፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ፤ ዙከርበርግ ፌስቡክ ጥሎት የነበረው እገዳ 'በመጪዎቹ ቀናት' እንደሚያበቃ እንደነገሯቸው ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አገሪቷ ላረቀቀችው ሕግ ማሻሻያ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ጆሽ ማክሰኞ እለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ "ፌስቡክ አውስትራሊያን ዳግም ተወዳጅታለች" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የታችኛው ምክር ቤት ረቂቅ ሕጉን ካፀደቀ በኋላ መንግሥት በረቂቅ ሕጉ ላይ እየተወያየ ነው።

ፌስቡክም አውስትራሊያ ያረቀቀችውን ሕግ ተከትሎ ዜናዎችን ከገጹ ላይ ለማገድ እንደሚገደድ አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል።

የመንግሥት የዜና ሕግ፤ ከፌስቡክና ከሌሎች የዜና ድርጅቶች ጋር በዜና ይዘት ዋጋ ላይ ፍትሃዊ የሆነ የድርድር ሒደት እንዲኖር ለማስቻል ያለመ ነው።

ይሁን እንጂ በፌስቡክና በጉግል ጥብቅ ተቃውሞ አስተናግዷል። ሁለቱም ኩባንያዎች ሕጉ ኢንተርኔት እንዴት እንደሚሰራ የተሳሳተ ግንዛቤ ወስዷል ሲሉ ተሟግተዋል። ፌስቡክም ከዜና ገጾች የሚያገኘው ገንዘብ ጥቂት መሆኑን ገልጿል።

ነገር ግን የአውስትራሊያ መንግሥት፤ ሕጉ በኢንተርኔት ዘመን ገቢያቸው እያሽቆለቆለ ለመጣው የዜና አታሚዎች 'የጨዋታ ሜዳውን' ለማስተካከል ያስፈልጋል ብሏል።

ፌስቡክ ሃሳቡን ለምን ለወጠ?

ፌስቡክ ማክሰኞ ዕለት እንዳለው ከመንግሥት ጋር ባደረገው ውይይት ስጋቱን ለማስወገድ ማረጋገጫ በማግኘቱ እንደሆነ ገልጿል።

በፌስቡክ የዓለም አቀፍ ዜና አጋርነት ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ካምቤል ብራውን፤ አነስተኛና የአገር ውስጥ አታሚዎችን ጨምሮ የመረጥናቸውን አታሚዎች ለመርዳት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰናል" ብለዋል።

ፌስቡክ በገጹ የራሱ የሆነ ምርቶቹን የሚያሳይበት ገጽ ያለው ሲሆን፤ ይህ ገጽ የሚዲያ ድርጅቶች ዜናዎቻቸውን እንዲያሰፍሩበት ይከፍላል። ይህ አሰራር ግን ያለው በዩናይትድ ኪንግደምና አሜሪካ ብቻ ነው።

ጉግልም ዋነኛ ሰርች ኢንጂን [ የመረጃ ማሰሻውን] ከአውስትራሊያ ሊያስወጣ እንደሆነ ሲገልጽ ነበር ። ይሁን እንጂ ድርጅቱ በቅርቡ ናይን ኢንተርቴይመንት፣ ሰቨን ዌስት ሚዲያን እና ሩፐርት መርዶክ የዜና ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋር ለመስራት ተስማምቷል።