ዩናይትድ ኪንግደም አን ሳን ሱ ኪ ከእስር እንዲፈቱ ልትጠይቅ ነው

የአን ሳን ሱ ኪ ምስል የያዙ ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ዶሚኒክ ራብ፤ አን ሳን ሱ ኪ ከእስር እንዲፈቱ ሊጠይቁ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ፤ በሚያንማር መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተመረጡትን መሪ አንግ ሳን ሱ ኪን ከእስር እንዲፈቱ ዛሬ በሚያደርጉት ንግግር ይጠይቃሉ ተብሏል።

ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ ጦሩ ከድርጊቱ ታቅቦ የሚያንማርን ዲሞክራሲያዊ ሂደት እንዲያከብር ጥሪ ያቀርባሉም ተብሏል።

ይህ የተሰማው የመፈንቅለ መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ለተቃውሞ አደባባይ በወጡበት ወቅት ቢያንስ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

ክስተቱ ከሁለት ሳምንታት በላይ በተካሄደው ተቃውሞ ያጋጠመ አስከፊ ግጭት ነውም ተብሏል።

ሚኒስትር ራብ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ መተኮስ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።

ግድያውን አስመልክቶ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ዲሞክራሲን በሚያደናቅፉ እና ሰላምን በሚያውኩት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር እንሰራለን” ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት ጦሩ አገሪቷን መቆጣጠሩና ሳን ሱ ኪን ለቁም እስር መዳረጉን ተከትሎ ተቃዋሚዎች አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

ጦሩ የአን ሳን ሱ ኪ ብሔራዊ ሊግ ለዲሞክራሲ ፓርቲ ባለፈው ዓመት ያሸነፈው በተጭበረበረ ምርጫ ነው ሲሉ ይከሳሉ።

ይሁን እንጂ ለዚህ ምንም ያቀረቡት ማስረጃ የለም።

ሳን ሱ ኪ ሕገ-ወጥ የፖሊስ መገናኛ ሬዲዮ በመያዝና የአገሪቷን የተፈጥሮ አደጋ ሕግ በመጣስ ክስ ቀርቦባቸዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሚያንማር ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን፣ የሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱና ጥቃቶች እየተፈፀሙ እንደሆነና ይህም በመረጃ የተያዘ መሆኑን ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሚኒስትሩ በሮሂንጂያንና በሌሎች አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ብሔሮች ላይ ያለው አደጋ መጨመሩን እንደሚገልፁ፤ እንደ ሳን ሱ ቺ ያሉ የሲቪል መሪዎች እንዲፈቱም እንደሚጠይቁ ተነግሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ‘አስቸኳይና ያልተነገረ’ ያሉትን በቻይና መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተባበሩት መንግሥታት እንዲመረምር ለመጠየቅ ይጠቀሙበታል ተብሏል።

ሚኒስትሩ ሩሲያ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አሌክሲ ናቫሊይ ላይ የፈፀመችውን “አሳፈሪ” ያሉትን እስርም ይተቻሉ።

ቻይና እና ሩሲያ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ አባል በመሆናቸው የሚኒስትሩን ንግግር በቀጥታ ያደምጣሉ ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት፤ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራትን አባል እንዲሆኑ በማድረጉ በስፋት ይተች የነበረውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ለመተካት የተቋቋመው እአአ 2006 ነው።

ምክር ቤቱ በዓመት ሦስት ጊዜ በመገናኘት የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ይገመግማል።

በሚያንማር፣ ሶሪያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ በሌሎች አገራት ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት የሚያደርግ የምርመራ ኮሚሽንም ያዋቅራል።