ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ኪምን "በኤር ፎርስ ዋን ልሸኝህ" ሲሉ ጠይቀዋቸው ነበር
ትራምፕ በሥልጣን ላይ እያሉ ከፈፀሟቸው ድርጊቶች መካከል ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ጋር የተገናኙበት ዕለት የሚረሳ አይደለም።
ቢቢሲ ይህንን ግንኙነት በተለመከተ ከሰሞኑ አዳዲስ መረጃዎች አግኝቷል። በውይይቱ ወቅቱ ነበሩ የተባሉ ሰዎችንም አናግሯል።
ዕድሜ ጠገብ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ብዙዎችን ያስደነገጠው ግን ትራምፕ ኪምን "በኤር ፎርስ ዋን ልውሰድህ" ሲሉ የጋበዙበት ቅፅበት ነው።
ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ከኪም ጋር የተገናኙት በቪዬትናም ከተማ ሃኖይ ነበር።
ይህ ግንኙነት ውጤቱ የሰመረ አልነበረም። ትራምፕ ለጋዜጠኞች "አንዳንድ ጊዜ የሚያዋጣው ሹልክ ብሎ መውጣት ነው ብለው ተናግረው ነው ከስብሰባው የወጡት።
ነገር ግን ስብሰባው ጥለው ከመውጣታቸው በፊት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት አንድ አስደናቂ ጥያቄ ለኪም አቅርበው ነበር።
በትራምፕ ዘመን በእስያ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ማቲው ፖቲንጀር "ትራምፕ ኪምን 'በኤር ፎርስ ዋን ወደቤትህ ልሸኝህ' ሲሉ ጋብዘዋቸው ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ፕሬዝደንቱ ኪም በቻይና በኩል አድርገው በባቡር እንደመጡ ያውቁ ነበር። 'በሁለት ሰዓት ውስጥ ወደ ሃገርህ ላደርስህ እችላለሁ' ቢሏቸውም ኪም ግን አሻፈረኝ አሉ።"
የቀድሞው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ጆን ቦልተን ይህ ክስተት በትራምፕና ኪም ፍቅር ወቅት ካይዋቸው አስገራሚ ነገሮች መካከል አስደናቂው እንደሆነ ለቢቢሲ ሹክ ብለዋል።
አማካሪው "ትራምፕ አዲስ የቅርብ ጓደኛ ያገኙ መስሏቸው ነበር" ይላሉ።
ትራምፕ በዚህ ምክክራቸው ወቅት የገዛ ዲፕሎማቶታቸውን ሳይቀር ያስደነገጥ አንድ ሌላ ነገር አድርገው ነበር።
የቀድሞው ፕሬዝደንት በኪም ጥያቄ መሠረት አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ ለማቆም ተስማሙ።
ቦልተን እንደሚሉት "ኪም ጁንግ ልክ እንደከዚህ በፊቱ በአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ መካከል ለ60 ዓመታት ያክል የዘለው ወታደራዊ ልምምድ እንዲቆም ነበር ፍላጎታቸው።"
"ትራምፕ ድንገት ተነስተው "ትራምፕ 'የጦርነት ጨዋታውን [ትራምፕ የተጠቀሙት ቃል] አስቆመዋለሁ። ምንም አስፋላጊ አይደለም፤ በዚያ ላይ ገንዘብ አባካኝ ነው። ይህ ደስተኛ እንደሚያደርግህ አምናለሁ' ሲሉ ማመን አቅቶኝ ነበር።"
"የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፖምፔዬ፤ የፕሬዝደንቱ ፅ/ቤት ኃላፊ ኬሊ እንዲሁም እኔ ክፍሉ ውስጥ ተቀምጠን ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ማንም አላማከረንም። ቀጥታ ከትራምፕ ጭንቅላት የመጣ ነገር ነው። ደግሞ በምትኩ ምንም ነገር አላገኘንም።"
ትራምፕ ለኪም የላኩት ምስጢራዊ መልዕክት
ኪምና ትራምፕ የተገናኙበት መድረክ ለብዙዎች ድንገቴ የሆነው ነበር።
ይህ ከመሆኑ ከወራት በፊት ትራምፕ ኪምን 'የሮኬቱ ሰውዬ' እያሉ ሲጠሩት፤ ሰሜን ኮሪያን ደግሞ 'እሳት አለብሳታለሁ' እያሉ ሲዝቱ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን የሆኑት ጄፍ ፌልትማን በዚህ ውጥረት ወቅት ከትራምፕ የተላከ ሚስጥራዊ መልዕክት ወደ ኪም እንዳደረሱ ይናገራሉ።
የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ፀሐፊ የሆኑት ጄፍ በሰሜን ኮሪያዎች ግብዣ ወደ ፒዮንግያንግ ሊያቀኑ ነበር።
ነገር ግን የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰውዬው ወደዚያ ማቅናታቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንዳይደለ ሲናገር ነበር።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ ዋይት ኃውስ መጡ።
ፌልትማን እንደሚሉት "በዚህ ወቅት ትራምፕ ወደ ጉቴሬዝ ጠጋ ብለው ጄፍ ፌልትማን ወደ ፒዮንግያንግ ቢያቀና መልካም ነው። ለሰሜን ኮሪያዎች እኔ ከኪም ጋር ለመጋናኘት ፈቃደኛ መሆኔን ይንገራቸው" ብለው ነበር።
ፌልትማን ወደ ፒዮንግያንግ ባቀኑ ወቅት ለሰሜን ኮሪያዊያን ሁኔታው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዳስረዷቸው ይናገራሉ።
የተመድ ባለሥልጣን ከትራምፕ የተሰጣቸውን መልዕክት ለኪም እንዲያደርሱሏቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጠየቋቸው።
"ከዚያ በክፍሉ ፀጥታ ሰፈነ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፀጥታውን ሰብረው 'እኔ አንተን አላምንህም። ለምንስ አምንሃለሁ? አሉኝ። እኔ እንዲያምኑኝ አልጠየቅኩም። ድርጅታችን ከትራምፕ መልዕክት ተልኮለታል። እኔ የመጣሁት መልዕክቱን ለማድረስ ነው አልኳቸው።"
ዲፕሎማቱ ወደ ፒዬንግያንግ ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ ጦርነት መነሳቱ አይቀሬ ነው እያሉ ይፈሩ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኪም ለትራምፕ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጡም።
ከወራት በኋላ ለደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸው ነገሯቸው።
የደቡብ ኮሪያው የደህንነት አማካሪ መልዕክቱን ለማድረስ ሳይውሉ ሳያድሩ ወደ ዋይት ኃውስ መጡ።
ትራምፕ ኪምን ለማግኘት 'እስማማለሁ' ባሉ ጊዜ የደቡብ ኮሪያው አምባሳደር ቹንግ በድንጋጤ ከወንበራቸው ሊወድቁ ትንሽ ነበር የቀራቸው ሲሉ የወቅቱ የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማክማስተር ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ልክ እንደ አብዛኛዎቹ የዋይት ኃውስ ሰዎች ማክማስተር ኪምና ትራምፕ መገናኘታቸው አልተዋጠላቸውም ነበር።
ነገር ግን ልክ እንደ አብዛኛዎቹ የውጭ ጉዳይ ውሳኔዎች ትራምፕ በራሳቸው መንገድ ነበር የተጓዙት ይላሉ አማካሪው።
"እኛ ሐሳባችን የነበረው ኪም ከመንግሥታት የሚመጣው ጫና ትንሽ እንዲከብድባቸው ነበር። ትራምፕ ግን ይህን ዕድል መቋቋም አልቻሉም"