ኮሮናቫይረስ፡ የጂ7 አገሮች ለክትባት ሥርጭት 7.5 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ገቡ

ታትሟል

የጂ7 አገራት መሪዎች ለኮሮናቫይረስ ክትባት ሥርጭት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደሚጨምሩ ተናገሩ።

ኮቫክስ የተባለውና ዓለም አቀፍ የክትባት ክፍፍሉን የሚያስተባብረው ጥምረትን ይበልጥ ለመደገፍም ቃል ገብተዋል።

አባል አገራቱ በበይነ መረብ ውይይት ካደረጉ በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ ባጠቃላይ 7.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ሃብታም አገራት ካላቸው የክትባት ክምችት ቀንሰው ለድሃ አገራት እንዲሰጡ እየተጠየቁ ነው።

ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ 4 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንደምትሰጥ ተናግረዋል። የጎርጎሮሳውያኑ 2021 ላይ ሁለት ቢኢዮን ዶላር፣ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ደግሞ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይሰጣል።

ጀርመን 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደምትሰጥም ተጠቁሟል። በተጨማሪም የአውሮፓ ሕብረት የሚያደርገውን ድጎማ እንደሚጨምር አስታውቋል።

ኮቫክስ 1.3 ቢሊዮን የክትባት ጠብታ ለአቅመ ደካማ አገሮች ለማከፋፈል እቅድ አለው። ኮቫክስን የሚመራው ጋቪ የዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎችም የጤና ተቋሞች ስብስብ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም፤ አገራትና ሕብረቶች ለክትባት ሥርጭቱ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አመስግነው፤ አሁንም ግን ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።

"የክትባት ክፍፍልን መደገፍ የሚበረታታው ትክክለኛው ውሳኔ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም አማራጩ መንገድ ስለሆነም ጭምር ነው" ብለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ አሜሪካ እና አውሮፓ ከክትባት ክምችታቸው 5% ለታዳጊ አገሮች እንዲሰጡ አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ የክትባት ሥርጭቱ ፍትሐዊ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

በዓለም ላይ 10 አገሮች ብቻ 75% ክትባት ሲያከማቹ የተቀሩት 130 አገራት ግን አንድም ጠብታ አልደረሳቸውም።

የጂ7 የወቅቱ መሪ ቦሪስ ጆንሰን አገራቸው ዩናይትድ ኪንግደም ክትባት ለድሃ አገራት እንደምትሰጥ አስታውቀዋል።

በመላው ዓለም 110 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ቢያንስ 2.4 ሚሊዮን ሞተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም፤ የተለያዩ አገሮች እና ሕብረቶች ለክትባቱ ድጋር ለመስጠት ቃል በመግባታቸው አመስግነዋል። ሆኖም ግን አሁንም ቃል ከተገባው በላይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ