ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ1.3 ቢሊየን ዶላር በላይ አጭበርብረዋል የተባሉ ሰሜን ኮሪያውያን አሜሪካ ውስጥ ተከሰሱ
በመላው ዓለም ከሚገኙ ባንኮችና የንግድ ተቋማት ከ1.3 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማጭበርበርና በግዳጅ ለመውሰድ ሞክረዋል የተባሉ ሶስት ሰሜን ኮሪያውያን አሜሪካ ውስጥ ክስ እንደተመሰረተባቸው ተገለጸ።
ሌላ የአሜሪካና ካናዳ ዜግነት ያለው ግለሰብ ደግሞ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ክስ ቀርቦበታል።
ከዚህ በተጨማሪ ግለሰቦቹ በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ ለደረሰው 'ዋናክራይ' በመባል ለሚታወቀው የበይነ መረብ ጥቃት ተሳታፊ ነበሩ ተብሏል። በወቅቱ በደረሰው ጥቃት የዩናይትድ ኪንግደም የጤና አገልግሎት ተሽመድምዶ ነበርም ተብሏል።
በግለሰቦቹ ላይ የቀረበውን ክስ ያነበቡት የአሜሪካው ብሄራዊ ደህንነት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጆን ዴመርስ ሰሜን ኮሪያ ''ብሄራዊ ባንዲራ ያለው ትልቅ የወንጀል ተቋም ሆናለች'' ብለዋል።
ክስ ከቀረበባቸው መካከል አንዱ የሆነው ፓርክ ጂን ህዮክ ደግሞ 2014 ላይ 'ሶኒ ኢንተርቴይንመንት ፒክቸርስ' ላይ ከተፈጸመው የመረጃ ጠለፋ ጥቃት ጋር በተያያዘ ከሁለት ዓመት በፊት ክስ ቀርቦበት ነበር።
የአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው ክስ የቀረበባቸው ሰሜን ኮሪያውያን በሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ደህንነት መስሪያ ቤት ስር በሚገኘው አጠቃላይ የስለላ ቢሮ ውስጥ እንደሚሰሩ አስታውቋል።
''ሰሜን ኮሪያ ተቀጣሪዎች ከሽጉጥ ይልቅ የክምፒዩተር መተየቢያ ኪቦርዶችን በመጠቀም በበይነ መረብ አማካይነት ገንዘብ እየዘረፉ ነው፤ በዚህም ምክንያት የዓለማችን ቁጥር አንድ የባንክ ቤት ዘራፊዎች ናቸው'' ብለዋል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ።
ሶስቱም ክስ የቀረበባቸው ግለሰቦች በአሁኑ ሰአት ሰሜን ኮሪያ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን አገሪቱ ደግሞ በአሜሪካ ክስ የቀረበባቸው ዜጎቿን አሳልፋ እንደማትሰጥ ካስታወቀች ቆይታለች።
የ37 ዓመቱ አሜሪካ ካናዳዊ ደግሞ ለቡድኑ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ያንቀሳቅስ ነበር የሚል ክስ ቀርቦበታል። ጋላብ ኣላማሪ የተባለው ግለሰብ በፍርድ ቤት ለቀረቡበት ከሶች በሙሉ ጥፋተኛ መሆኑን ለማመን ተስማምቷል።