በሚየንማር የምሽት አሰሳዎችና እስሮች ቀጥለዋል ተባለ

ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሚየንማር ባለስልጣናት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱን የሚቃወሙ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሌሊት የሚያደርጉትን ድንገተኛ አሰሳ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች መቃወማቸውን ቀጥለውበታል።

በቅርቡ በተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ የአገሬው ዜጎች ወታደሮች አሰሳ በሚያደርጉበት አካባቢ የሚገኙ ጎረቤቶቻቸውን ጎርጓዳ ሰሀን እና መጥበሻዎችን በመደብደብ የጥንቃቄ ከእንቅልፋችሁ ንቁ መልዕክት ሲያስተላልፉላቸው ታይቷል።

በፈረንጆቹ የካቲት 1/2021 ላይ ወታደሮች አገሪቱን ስልጣን በኃይል ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የደቡብ ምስራቃዊቷ አገር ዜጎች ተቃውሟቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

ቅዳሜ ዕለት ወታደራዊው መንግስት እንዳስታወቀው ተቃውሞውን የሚመመሩ ሰባት ወሳኝ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የማሰሪያ ትዕዛዝ ወጥቷል።

በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተባሉት ግለሰቦች በአገሪቱ እምብዛም ጥቅም ላይ ሲውል በማይታየው ''ሰላምን የማደፍረስ' ክስ ሲሆን የቀረበባቸው ከመካካለቻው ሚን ኮ ኒያንግ ይገኝበታል። በአውሮፓውያኑ 1988 በነበረው የተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መሪ ከሚባሉት ተማሪዎችም መካከል ነበር።

በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ብቅ ብሎም ወታደሮች በሌሊት እየዞሩ ሰዎችን ከቤታቸው የሚይዙት ነገር መቆም እንዳለበትና በእጅጉ እንደሚቃወመው አስታውቆ ነበር።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ባሳለፍነው አርብ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ከ350 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መፈንቅለ መንግሥቱ ከተካሄደ በኋላ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በምርጫ ያሸነፉት የአገሪቱ መሪ አንግ ሳን ሱ ቺም ቢሆኑ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ባለፈው ሕዳር በተደረገ ምርጫ የሳን ሱ ቺ ፓርቲ 'ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ' መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን የመቀመጫ ቁጥር ማግኘት ችሎ ነበር። ሆኖም ወታደሮቹ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ ቆይተዋል።

ሳን ሱ ቺ በአንድ ወቅት ለዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ትልቅ ተምሳሌት ተደርገው ነበር የሚታዩት። ምክንያቱም ምሕረት አያውቁም ከሚባሉት የምያንማር ወታደራዊ ኃይሎች በተጻጻራሪ በመቆም በአገሪቱ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በመታገል ረዥም ዓመታት አሳልፈዋል።

ይህን ተከትሎም በ1991 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፍ ችለው ነበር። ሽልማቱን ያሸነፉት በቁም እስር ላይ ሳሉ ነበር። ሳን ሱ ቺ ለ15 ዓመታት በእስር ከቆዩ በኋላ በ2010 ነጻ ተደርገዋል።

በ25 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ ምርጫም ፓርቲዋ ትልቅ ድል አግኝቶ ወደ ሥልጣን መምጣት ችለው ነበር።

ሆኖም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሳን ሱ ቺ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ አይፈቅድም። ምክንያቱም ልጆቿ የውጭ ዜጎች ስለሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ መንግሥትን የምትመራው ከጀርባ ሆነው ነው።

ወታደራዊ መንግስቱ ቅዳሜ ዕለት ሰዎች ሳይከሰሱ ከ24 ሰአታት በላይ ማሰር እና ያለፍርድ ቤት ፈቃድ የሰዎችን የግል ንብረት መበርበር የሚከለክለውን ሕግ እንደሻረው አስታውቋል።

የቢቢሲዋ ዘጋኒ ኒዬን ቻን አዬ እንደሚለው ሚየንማር ሰላማዊ እንቅልፍ ማግኘት ብርቅ እየሆነ መጥቷል።

ወታደሮችና ፖሊሶች በድንገት የማንኛውንም ግለሰብ ቤት በሌሊት ሰብረው ሊገቡ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ዜጎች ቁጭ ብለው ሌሊቱን ሙሉ እየተጋገዙ ሲጠብቁ ያድራሉ።

በሚየንማር የአንድነት ቀን ሲከበር ኃላፊው ጀነራል ሚን አውግ ህላግ "አገራዊ አንድነት ያስፈልገናል" ቢሉም ሕዝቡ አን ሳን ሱ ቺን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ከቁም እስር እንዲለቀቁ እየጠየቀ ነው።

በሚየንማር የአንድነት ቀን ሲከበር ወታደራዊ ኃይሉ 55 የውጪ ዜጎችን ጨምሮ 23,000 ታራሚዎችን ከእስር ለቋል።