ጋዜጠኛ አስፈራርቷል የተባለው የፕሬዚዳንት ባይደን ረዳት ከስራ ለቀቀ

ቲጄ ዱክሎ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በዋይት ሃውስ ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ቲጄ ዱክሎ ሴት ጋዜጠኛን አስፈራርቷል በሚል ያለ ክፍያ ከስራ እንዲታገድ ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ ከኃላፊነት ቦታው እንደለቀቀ አስታውቋል።

ፖለቲኮ የተባለው ህትመት ጋዜጠኛ የሆነችው ታራ ፓልመሪ ስለ ግለሰቡ የግል ህይወት ጥያቄዎችን በመጠየቋ "አጠፋሻለሁ" በሚል አስፈራርቷታል ተብሏል።

በትናንትናው ዕለት ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪው የተጠቀመበት ቋንቋ "አፀያፊ" መሆኑን በማመን መግለጫ ሰጥቶ ነበር።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአስተዳደራቸው ውስጥ የስራ አጋሮቻቸውን ለሚያዋርዱ ግለሰቦች ምህረት እንደማያደርጉና እንደሚያባርሩ ቃል ገብተው ነበር።

ቲጄ ዱክሎ ጋዜጠኛዋን አስፈራርተሃል በሚል ከስራ የታገደው በዚሁ ሳምንት አርብ እለት ነበር።

የፖለቲኮዋ ጋዜጠኛ ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪው የባይደንን የምርጫ ቅስቀሳ ከዘገበው የአክሲዮሱ ጋዜጠኛ አሌክሲ ማክካሞንድ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ የምርመራ ዘገባ እየሰራች ነበር ተብሏል።

በምላሹም ቲጄ ጋዜጠኛዋ ጋር ደውሎ "አጠፋሻለሁ" ያላት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የሚያዋርዱና፤ የሴትነት ክብርን የሚነኩ ስድቦችን መስደቡን ቫኒቲ ፌይር ዘግቧል።

የ32 አመቱ ቲጄ ዱክሎ በበኩሉ "ባሳየሁት አስጠሊታ ባህርይ የተሰማኝ እፍረትና ፀፀት በቃላት የሚገለፅ አይደለም" በማለት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

"የትኛዋም ሴት ብትሆን ከማንኛውም ሰው መስማት የማትፈልገውን ቃል ተጠቅሜያለሁ። በተለይም ስራዋን እየሰራች ያለች ግለሰብ ላይ እንዲህ አይነት አፀያፊ ቃል መጠቀሜ አሳፋሪና ተቀባይነት የሌለው ነው" ብሏል።

አክሎም " በስራዬ የዋይት ሃውስ የስራ ባልደረቦቼንና ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን በማሳፈሬ ተሸማቅቄያለሁ። ይህንንም ተከትሎ ከዋይት ሃውስ የኮሙዪኒኬሽን አመራር ጋር ባደረግኩት መሰረት ከስራዬ ለቅቄያለሁ" በማለት አስፍሯል።

የፕሬዚዳንት ባይደን ቃለ አቀባይ ጄን ሳኪ በበኩላቸው "ይህ ያልተገባ ባህርይ መሆኑን መጀመሪያ ያመነው ቲጄ ነው። በፕሬዚዳንት ባይደን ዘንድም ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

ቃለ አቀባይዋ አክለውም ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪው የመልቀቅ ውሳኔው ላይ የደረሰው ከዋይት ኃውስ ኃላፊ ሮን ክላይን በተሰጠው ድጋፍ መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

ጋዜጠኛዋ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ አስተያየት አልሰጠችም።