የትዊተር እና የሕንድ መንግስት እሰጥ አገባ

ትዊተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትዊተር
ታትሟል

በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት አንድ ከፍተኛ የህንድ ባለስልጣን ከማህበራዊ ሚዲያው ትዊተር ዓለማቀፍ ስራ አስፈጻሚዎች ጋር በበይነ መረብ አማካይነት ስብሰባ አካሂደው ነበር።

ትልቁ የማህበራዊ ሚዲያ ተቋም ትዊተር ሕንድ ውስጥ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከፈለገ የሕንድ በር ክፍት እንደሆነና ነገር ግን የአገሪቱን ሕግ ማክበር እንዳለበት ተነግሮታል።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር የናሬንድራ ሞዲ ፓርቲ 'ብሃራቲያ ጃናታ' እና ትዊተር እሰጥ አገባ ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል። የሕንድ ገበሬዎች የግብርና ዘርፉ ላይ ተግባራዊ የተደረገውን አዲስ ሕግ በመቃወም ላይ የሚገኙ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ይህንኑ በመደገፍ በትዊተር ዘመቻ ጀምረዋል።

በአውሮፓውያኑ ጥር 26/2021 መጀመሪያ ላይ ሰላማዊ የነበረው የገበሬዎች የተቃውሞ ሰልፍ መልኩን ቀይሮ አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የሕንድ መንግስት ከገበሬዎቹ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተላለፉትን መልዕክቶች ትዊተር እንዲያጠፋ እንዲሁም በሲክህ አማጺያን እና በፓኪስታን በሚደገፉ ቡድኖች ጥቅም ላይ የሚውሉ ትዊተር ገጾችን እንዲያግድ ጠይቋል።

የሕንድ መንግሥትን ክስ ተከትሎም ትዊተር 250 የሚደርሱ የትዊተር ገጾችን ያገደ ሲሆን በምክንያትነት ያቀረበው ደግሞ የሕዝብ ሰላምን ለማስጠበቅ በሚል ነበር። የትዊተር ገጻቸው ከታገደባቸው መካከል ደግሞ የምርመራ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች የሚገኙበት ሲሆን ከስድስት ሰአታት በኋላ የነዚህ ሰዎች ገጽ ተመልሶ ተከፍቶላቸዋል።

የሕንድ ገበሬዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሕንድ ገበሬዎች

ትዊተርም የሕንድ መንግሥት ያቀረበው በቂ ያልሆነ ምክንያት ነው ብሏል።

ይህን ተከትሎም የናሬንድራ ሞዲ መንግስት ደስተኛ አልሆነም። መንግሥት ባወጣው ጠበቅ ያለ መግለጫም ትዊተር የከፈታቸውን ገጾች በፍጥነት እንዲዘጋ አልያም እንዲያግድ ጠይቋል። ይህ የማይሆነ ከሆነ ግን በሕንድ የሚገኙ የትዊተር ተቀጣሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። እስከ 7 ዓመት የሚደርስ እስር ሊጠብቃቸው እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

የሕንድ መንግሥት እንደሚለው በትዊተር የተላለፉት መልዕክቶች ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ ሆን ተብሎ ውጥረት ለማንገስ የተደረጉ ዘመቻዎች ናቸው።

ረቡዕ ዕለት ትዊተር ባወጣው መግለጫ ከ500 በላይ ገጾችን እንዳገደና አንዳንዶቹ እንደውም እስከመጨረሻው የታገዱ መሆናቸውን አስታውቆ፣ የትዊተርን ሕግ የሚጥሱ ማንኛውም አይነት ገጾችን ከመዝጋት ወደኋላ እንደማይል ገልጿል።

ነገር ግን በመገናኛ ብዙሀን ስር የሚተዳደሩ የትዊተር ገጾችን፣ የመብት ተሟጋቾች ገጾችን እንዲሁም የፖለቲከኞችን ገጾች እንደማያግድና የውስጥ አሰራሩን እንዲሁም መመሪያዎቹን እንደሚጣረስ አስታውቋል።

ይህን ተከትሎ በትዊተር እና በሕንድ መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት ከፍ ብሏል። የሕንድ የመረጃ ሚኒስትሩ ሐሙስ ዕለት በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው የተዛባ መረጃ እና ሃሰተኛ ዜና የሚያሰራጩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጠበቅ ያለ ርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

''ሕንድ ውስጥ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሏችሁ፤ እዚህ አገር ቢዝነስ ለመስራት ማንም አያግዳችሁም፤ ነገር ግን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ማክበር አለባችሁ'' ሲሉ ተደምጠዋል ሚኒስትር ራቪ ሳንካር ፕራሳድ ፌስቡክ እና ትዊተርን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሰው።

የሕንድ ሕገ መንግሥት መሰረት ማንኛው የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል የበይነ መረብ መልዕከትን መንግስት መዝጋት እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል።

ባለፉት ዓመታት ሕንድን ጨምሮ አምስት አገራት በትዊተር የተላለፉ መልዕክቶች ይጥፉልን ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል። ጃፓን፣ ሩሲያ፣ ቱርክ እና ደቡብ ኮሪያ ቅሬታቸውን ካቀረቡት መካከል ናቸው።

እነዚህ አምስት አገራት ለትዊተር ከቀረቡት ቅሬታዎች መካከል 96 በመቶ የሚሆነውን የሚይዙ ሲሆን ከሕንድ ብቻ 5 ሺ 900 ቅሬታዎች ቀርበዋል።

ሕንድ ውስጥ እስከ 15 ሚሊየን የሚደርሱ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚነገርለት ትዊተር፣ በቀላሉ እጁን የሚሰጥ አይምስልም። "የሰዎችን በነጻነት ሃሳብ የመግለጽ መብት አሁንም እናበረታታለን። በሕንንድ ሕግ መሰረት የተለያዩ አማራጮቸን እየፈለግን ነው" ብሏል ድርጅቱ።