የኔልሰን ማንዴላን ቀብር ከማስፈፀም ጋር በተያያዘ ገንዘብ አጭበርብረዋል የተባሉ ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በደቡብ አፍሪካ እኤአ በ2013 ህይወታቸው ያለፈውን ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላን ቀብር ከማስፈፀም ጋር በተያያዘ ሙስና ፈጽማችኋል የተባሉ ክስ ተመሰረተባቸው።
ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ቀደምት አባል የሆኑ ግለሰብ ይገኙበታል።
ግለሰቡ በቀረበባቸው ውንጀላ ላይ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጡም።
አቃቢያነ ሕጎች ግን ግለሰቦቹን 700 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በመመዝበር እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ወንጀል መጠርጠራቸውን ተናግረዋል።
ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ በ1994 ከወደቀ ወዲህ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ነበሩ።
ይህ የሙስና ወንጀል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው ማንዴላ ከሞቱ ወራት በኋላ እኤአ በ2014 ነው።
ፕሬዝዳንት ማንዴላ ህይወታቸው በ2013 ያለፈ ሲሆን በቀብራቸው ላይም ከመላው አለም የተሰባሰቡ የተለያዩ አገራት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች ታድመዋል።
የሙስና ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው ሰዎች መካከል የምስራቃዊ ኬፕ አውራጃ የጤና ሚኒስትር ኃላፊ ሲድዲሲዋ ጎምባ፣ በርካታ የንግድ ሰዎች እና የገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ አባል የሆኑ ህግ አውጪዎች ይገኙበታል።
አቃቢያነ ሕጎች የገንዘብ ማጭበርበሩ የተፈፀመው ቀብሩን ለመታደም የተገኙ ሰዎችን ለማጓጓዝ እና ለአዳራሾችና አደባባዮች ክፍያ በሚል መሆኑ ገልፀዋል።
ተከሳሾቹ ዋስትና የተፈቀደላቸው ሲሆን በመጋቢት የመጀመሪያ ሳምንት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል።
ኔልሰን ማንዴላ ከአፍሪቃ ዋነኛ የነጻነት ተምሳሌቶች እና ታጋዮች መካከል አንዱ ናቸው። የነጭ አገዛዝን እምቢኝ በማለታቸው ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ያክል እስር ቤት ቆይተዋል።
















