ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የዩኬ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በአሜሪካ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው ተባለ
እንግሊዝን እያስጨነቃት ያለው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በአሜሪካም በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል።
በከፍተኛ መጠን የመተላለፍ ባህርይ አለው የተባለው ይህ ዝርያ በአሜሪካ በባለፉት ቀናት በእጥፍ እየተስፋፋ መሆኑን ይኼው ጥናት አስታውቋል።
የዝርያው የመስፋፋት ፍጥነት ቢ1117 የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን በአለም አቀፉ የክትባት ሂደቶችም ላይ ከፍተኛ ጫና አሳርፏል ተብሏል።
የአሜሪካው የበሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል (ሲዲሲ) የዩኬው የኮሮናቫይረስ ዝርያ በመጋቢት ወር ዋነኛው ኮሮና ይሆናል በማለት ተንብይዋል።
ጥናቱ የተለያዩ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች የተጣመሩበት ሲሆን ሜድርክሲቭ በተባለ ድረገፅም ላይ ወጥቷል።
በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአሜሪካ አሁንም ትንሽ ነው ተብሏል።
የአዲሱ ዝርያ ከተመዘገበባቸው ግዛቶች መካከል ፍሎሪዳ የምትመራ ሲሆን ካሊፎርኒያ ትከተላለች።
"ጥናታችን እንደሚያሳየው ሌሎች አገሮች ላይ ቢ117 በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ዋነኛው የኮቪድ-1ዝርያ መሆን እንደቻለው እኛም ወደዛ እየገሰገስን ነው። የኮሮናቫይረስን አስከፊነትና ገዳይነት ለመቀነስ አስቸኳይና ወሳኝ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉም ማሳያ ነው" ብለዋል የሪፖርቱ ፀሃፊዎች።
በሪፖርቱ መሰረት አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ከቀድሞው በበለጠ 35-45 በመቶ ብልጫ ፍጥነት ይተላለፋል።
ሲዲሲ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ መኖሩን ባሳወቀበት ባለፈው ወር ከሚመዘገቡት ህሙማን ቁጥር በአዲሱ ዝርያ የተያዙት 0.5 ያነሰ ቢሆን በቅርቡ ግን ከ3.6 በመቶ በላይ በፍጥነት እየገሰገሰ እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፥
በአሜሪካ በየቀኑ የሚመዘገበው የህሙማን ቁጥር ከባለፈው ወር ጀምሮ መቀነስ ቢያሳይም የሟቾች አማካይ ቁጥር አሁንም እንዳሻቀበ ነው።
በአገሪቷ በየቀኑ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ 3 ሺህ ሰዎች የሚሞቱ ሲሆን ሆስፒታሎችም የህሙማኑን ከፍተኛ ቁጥር ለማስተናገድ ተቸግረዋል ተብሏል።
ቢቢ117 የሚል ስያሜ የተሰጠውና በመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝ የተገኘው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ወደ አምሳ አገራት ተዛምቷል።
ልክ እንደ ቀድሞው ቫይረስ ለአዛውንቶችና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ሰዎች የበለጠ አደጋ አለው።
አዲሱ ዝርያ ከ30 በመቶ በላይ ለሞት ያጋልጣል ቢባልም የተሰጡት ማስረጃዎች ጠንካራ እንዳልሆኑ ተነግሯል።
በአሁኑ ሰዓት ያሉ ክትባቶች ቀደም ላሉት የቫይረሱ ዝርያዎችን እሳቤ ውስጥ ከተው ቢሆንም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፋይዘር፣ ኦክስፎርድ አስትራዜንካና ሞደርና ክትባቶች ከቢቢ117 ዝርያ ይጠብቃሉ።