ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኒውዮርክ ሐኪሞች የመጀመርያውን የተሳካ የፊትና የእጅ ንቅለ ተከላ አደረጉ
በኒውዮርክ በዓለም የመጀመርያ የተባለለት ስኬታማ ሙሉ የፊትና የሁለት እጆች ንቅለ ተከላ አደረጉ፡፡
የፊትና የእጆች ንቅለ ተከላ የተደረገለት ሰው የ22 ዓመቱ ጆ ዲሚዮ ይባላል፡፡
ንቅለ ተከላው ድፍን 23 ሰዓታትን የፈጀ ሲሆን 140 የጤና ባለሙያዎች ርብርብ ያደረጉበት ነበር ተብሏል፡፡
በፈረንጆቹ 2018 ነበር ጆ ዲሚዮ በመኪና አደጋ 3ኛ ደረጃ ቃጠሎ ፊትና እጁ ላይ የደረሰበት፡፡ 80 ከመቶ የሚሆነው ሰውነቱ በእሳት ተለብልቦ ነበር፡፡
80 ከመቶ ቃጠሎ የደረሰበት ሰው በሕይወት የመቆየት ዕድሉ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡
በዚህ አሰቃቂ የመኪና አደጋ ወጣቱ የእጆቹ ጫፎች ተቆራርጠዋል፣ ከንፈሩና የዐይን ክዳኑ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከንቅለ ተከላው በኋላ ጆ ዲሚዮ "ሕክምናውን ለ2ኛ ጊዜ የመኖር ዕድል ሰጥቶኛል" ሲል ደስታውን ገልጧል፡፡
ጆ ዲሚዮ አደጋው የደረሰበት ከምሽት ፈረቃ ተረኛ ሥራው ወደ ቤቱ በማታ እየመጣ የድካም እንቅልፍ ጥሎት የመኪናው መሪ ላይ ሳለ አሸልቦት ነው፡፡
በዚያ ሸለብታ ወቅት የሚያሽከረክራት መኪና ከቁጥጥር ውጭ በመውጣት ከተጋጨች በኋላ ወዲያውኑ በእሳት ስለተያያዘች ነበር ጆ ዲሚዮ 80 ከመቶ ሰውነቱ በእሳት የተበላው፡፡
ከዚያ በኋላ ለአራት ወራት ያህል የእሳት ቀጠሎ ተጎጂዎች የሚያገግሙበት ጽኑ ሕሙማን ክፍል የቆየ ሲሆን በአብዛኛው ጊዜ ራሱን እንደሳተ ነበር ያሳለፈው፡፡
ጆ በትንሹ ወደ 20 የሚደርሱ ቀዶ ጥገናዎችን በተከታታይ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ፊቱና እጁ ላይ የተደረጉ ቀዶ ጥገናዎች ለውጥ ያመጡ አልነበሩም፡፡
በመጨረሻ በ2019 ዓ/ም የኒውዮርክ የሕክምና ትምህርት ቤት ማዕከል (New York, NYU Langone) ለከፍተኛ ንቅለ ተከላ ሙከራ እንዲገባ ተደረገ፡፡
ባለፈው ነሐሴም ይህንን በታሪክ ለ3 ጊዜ ብቻ የተሞከረ የፊትና የእጅ ንቅለ ተከላ ማድረግ ቻለ፡፡ ይህን የሆነውም በዚህ የኒውዮርክ የሕክምና ማዕከል ውስጥ ነበር፡፡
ጆ የፊትና የሁለት ክንዶችና ጣቶችን ያገኘው ከለጋሽ ነው፡፡
የፊት ንቅለ ተከላ መርሐግብር ዳይሬክተር የሆኑት ኤድዋርዶ ርድሪጉዝ "የተሻለ መልክ እንዲኖረው ብቻ አይደለም ያስቻልነው፤ እጇቹን መልሶ እንዲጠቀምም አስችለነዋል" ብለዋል፡፡
ጆ ዲሚዮ ይህን ንቅለ ተከላ ካደረገ በኋላ ለ45 ቀናት በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
ጆ ከሰው በልገሳ የተሰጠውን አዲሱን የፊት ገጽታ ለመቀበል እየጣረ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ አዲስን ማንነቴንም እየተዋወቅኩት መጥቻለው ብሏል፡፡
ጆ ከንቅለ ተከላው በኋላ ለሌላ 2 ወራት በሆስፒታሉ ቆይቷል፡፡
በዚህ ቆይታውም ነበር እጁን እንዴት በድጋሚ መጠቀም እንዳለበት የተማረው እና የዓይን ሽፋኑን መክደንና መክፈት የተለማመደው፡፡
ከዚህ ቀደም የፊትና የሁለት እጆች ንቅለ ተከላ በዘመናዊ ሕክምና ታሪክ ተደርጎ ያውቃል፡፡ ይህም ለ2 ጊዜ ብቻ ሲሆን ጆ በዓለም ይህን በማድረግ 3ኛው ታካሚ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ስኬታማ ሲሆን የጆ ዲሚዮ በምድራችን የመጀመርያው ነው፡፡
ከዚህ ቀደም አንድ ታካሚ ንቅለ ተከላው ከተደረገላቸው በኋላ በሕክምናው ውስብስብነት የተነሳ የሞቱ ሲሆን ሌላ ታካሚ ደግሞ የተገጠሙለት እጆች እንደታሰበው ሊሰሩለት ስላለችሉ እንዲወገዱ ሆነዋል፡፡
ምንም እንኳ ንቀለ ተከላው የተደረገው ባለፈው የነሐሴ ወር ቢሆንም ሐኪሞች በጉዳዩ ዙርያ ዝምታን የመረጡት ስኬታማ መሆኑን እርግጠኛ እስኪሆኑ ነበር፡፡
ሚስተር ሮድሪጓዝ እንዳሉት ታማሚው በቀን ለ5 ሰዓታት ቀላል የማገገምያ እንቅስቃሴዎች ይሰራ እንደነበረና እስከዛሬ በሕይወት ዘመናቸው ካጋጠሟቸው ታማሚዎች ሁሉ እጅግ ከፍ ያለ ጥንካሬና ጽናት ያለው ታማሚ ነበር ሲሉ አድንቅውታል፡፡
‹‹ተነስቶ ጎልፍ መጫወትን ይፈልጋል፣ ስፖርት መሥራት ይፈልጋል፣ የሚያነሳቸው የስፖርት የክብደት ሚዛኖች ቀላል አይደሉም፤ አስደናቂ ልጅ ነው› ብለዋል፡፡
ዳ ሚዮ አሁን ራሱን ችሎ እንደሚንቀሳቀስና ቁርስ አብስሎ መብላት እንደጀመረ ተናግሯል፡፡
"ይህ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚገኝ ስጦታ ነው፡፡ የለጋሼ ከፊል እኔ ውስጥ አለ፡፡ ይህ ለለጋሼ ቤተሰቦች ምቾትን የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡ እኔና ወላጆቼ ለተደረገልን ሁሉ፣ ለተሰጠኝ 2ኛ የመኖር ዕድል ከልብ አመሰግናለሁ" ብሏል፡፡