ሻምፒዮንስ ሊግ፡ ስሊቨርፑል ለሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ወደ ጀርመን መጓዝ አይችልም ተባለ

ታትሟል

ሊቨርፑል ለሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ወደ ጀርመን መጓዝ አይችልም ተባለ።

ሊቨርፑል ከጀርመኑ አርቢ ሊፕዚሽ ክለብ ጋር በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሊያደርገው የነበረውን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ወደ ጀርመን አቅንቶ ማካሄድ እንደማይችል ተገልጿል።

ሊቨርፑል ቀደም ብሎ በወጣው መርሃ ግብር መሠረት ከሳምንት በኋላ በየካቲት 9 የመጀመሪያ ዙር ጨዋታውን ከጀርመኑ አርቢ ሊፕዚሽ ጋር ማድረግ ነበረበት።

ነገር ግን ጀርመን ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አዲሱ የኮሮናቫይረስ በስፋት ከተዛመተባቸው አገራት የሚመጡ መንገደኞች ላይ የጉዞ እገዳ ጥላለች።

የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር መግለጫ እንደሚያሳየው የጨዋታ መርሃ ግብሩ የተቀመጠውን መስፈረት የሚያሟላ እንዳልሆነ ለአስተናጋጁ ክለብ ተነግሮታል ብሏል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር ስለጉዳዩ ከክለቡ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።

በሁኔታው ዙሪያ ያሉ አዳዲስ የሃሳብ እድገቶች እየቀረቡለት በተስፋ እንዲጠባበቅ ክልከላ የተጣለበት ሊቨርፑል ተነግሮታል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በአውሮፓ ሊግ እና አውሮፓ ሻምፕዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የመመሪያ ለውጥ አድርጓል።

በዚህም ምክንያት በአንዱ አገር ውስጥ የጉዞ ክልከላ ከተደረገ ጨዋታው አይደረግም ማለት ነው። "አስተናጋጁ ክለብ ተስማሚ የሆነውን አማራጭ ማቅረብ ይችላል፤ ምናልባትም ገለልተኛ በሆነች አገር ሊሆን ይችላል" ይላል የተሻሻለው መመሪያ።

ነገር ግን ጨዋታውን በሌላ ሜዳ እና በሌላ ቀን ማካሄድ አይፈቀድም። አስተናጋጁ ክለብ ይህን ማድረግ ከተሳነው ተስተናጋጁ ክለብ የሦስት ለምንም ፎርፌ ውጤት ይሰጠዋል ይላል የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የተሻሻለው መመሪያ።

ጀርመን እገዳውን እስከ የካቲት 10 የምታቆይ በመሆኑ ምናልባት እንደአማራጭ ሊቨርፑል የመጀመሪያውን ጨዋታ በሜዳው እንዲያደርግ እና ወደ ጀርመን ከሚጓዝ ይልቅ የጀርመኑን ክለብ ሊጋብዝ ይችላል ተብሏል።

ሁለተኛው የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚከናወነው በመጋቢት አንድ ነው። ይህኛውን አማራጭ ክለቦቹ የሚጠቀሙ ከሆነ ሊቨርፑል ወደ ጀርመን የሚጓዘው መጋቢት አንድ ይሆናል ማለት ነው።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሚመረጠውን ገለልተኛ አገር ሜዳ የመወሰን እና የጨዋታዎቹን ጊዜ የመወሰንና የማስተካከል ስልጣን ያለው ብቸኛው አካል መሆኑን መመሪያ ይደነግጋል። ገለልተኛ ተብሎ የሚመረጠው አገርም የእግር ኳስ ማሕበሩ በሚሰራባቸው አገራት ውስጥ የተካተተ መሆን አለበት ይላል።