ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስዊድናዊቷ ነርስ ደሴት ለብቻዋ ተለቆላት 60 ፊልሞችን ልትመለከት ነው
ስዊድናዊቷ ነርስ ደሴት ለብቻዋ ተለቆላት 60 ፊልሞችን ልትመለከት ነው፡፡
ነርሷ ይህን ዕድል ያሸነፈችው በስዊድኗ 2ኛ ከተማ በጎተቦሬ (ጉተንበርግ) የሚደረገውን የፊልም ፌስቲቫል በማሸነፏ ነው፡፡
ሊዛ ኤርኖት ይህንን ውድድር ያሸነፈችው ከ12ሺህ የፊልም አፍቃሪዎች መሀል ተወዳድራ ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ይህን ዕድል ያመለከቱት ከስዊድን ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም አመልክተው ነው፡፡
በፌስቲቫሉ የሚቀርቡት 60 ፊልሞች ናቸው፡፡
ነርሲቱ ፊልሞቹን የምትመለከተው ከስዊድን ጠረፍ በምትገኝ ደሴት ቁጭ ብላ ላይትሐውስ ውስጥ በመቀመጥ ነው፡፡
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ነርሷ በሆስፒታል ውስጥ የኮቪድ ታማሚዎችን ስትንከባከብ የነበረች ጀግኒት እንደነበረች ተነግሯል፡፡
"አሁን ብቻዬን ከሰዎች ገለል ብዬ መዝናናት እፈልጋለሁ፡፡ የተለየ ሁኔታ ውስጥ መሆን ነው የምሻው" ስትል ተናግራለች፡፡
የፌስቲቫሉ አሰናጆች ወትሮ ብዙ ሺህ ሕዝብ የሚገኝበትን ይህን የፊልም ትእይንት በወረርሽኙ ምክንያት ሊያካሄዱት አልቻሉም፡፡
በሲኒማ ቤቶች የሚታዩ ፊልሞችም አይኖሩም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሁሉም የፊልም ፌስቲቫሉ ኩነቶች በቀጥታ በበይነ መረብ ይተላለፋሉ ብለዋል፡፡
የዚህ ፌስቲቫል አሰናጆች ላለፉት ወራት አንድ እውነተኛ የፊልም ወዳጅ ሰው ሲያፈላልጉ ነበር፡፡ አሸናፊው ሰው ብቻውን አንድ ደሴት ላይ ቁጭ ብሎ 60 ፊልሞችን ለመመልከት በሥነ ልቡና እና በስሜት ዝግጁ የሆነ መሆን ይኖርበታል ብለው ነበር፡፡
ነርስ ሊዛ ኤንሮት የኮቪድ ታማሚዎችን በመንከባከብ ጉልበቷ እንደተሟጠጠና አሁን ግን ለአንድ ሳምንት እፎይ ማለት እንደምትሻ ለቢቢሲ የስቶክሆልም ዘጋቢያችን ማዲ ሳቪጅ ነግራታለች፡፡
ነርሲቱ ፓተር ኖስተር ላይትሐውስ ሐምነስካር በምትባል ደሴት የምትቆየው ያለምንም ቴክኖሎጂያዊ ቁሳቁሶች ነው፡፡ ስልክ፣ ኮምፒውተር፣ መጻሕፍትንም ሆነ ሌላ ጊዜ ለማሳለፍያ የሚሆን ነገር መያዝ አይፈቀድላትም፡፡
‹‹ንፋሱ፣ ባሕሩ እና በደሴት ብቻዬን መሆን ይህ ሁሉ እጅግ ልዩ ስሜት ውስጥ የሚከተኝ ነው የሚሆነው›› ብላለች ነርስ ሊዛ፡፡
ሊዛ በብዛት የኖረችው ስኮቭዴ በምትባል የጎተቦርግ ምሥራቅ የምትገኝ ትንሽዬ ከተማ ውስጥ ነው፡፡
በዚች ትንሽ ከተማ ውስጥ የአንድ የፊልም ወዳጆች ማኅበርም አባል ናት፡፡
ትናንት ቅዳሜ ሊዛ ወደ ደሴቲቱ በታንኳ የተወሰደች ሲሆን ይቺ ደሴት በስዊድን ጠረፍ ከማርስትራንድ ቅርብ የምትገኝ ናት፡፡
ሊዛ በደሴቲቱ የምታሳልፈው ጊዜ በቪዲዮ ለዓለም ይተላለፋል፡፡
የዚህ ታላቅ የፊልም ፌስቲቫል ዋና አሰናጅ ሚሪያ ዌስተርን ይህን ልዩ ዕድል ለአንዲት የኮቪድ ጀግና መስጠታችን የሚገባ ብቻም ሳይሆን ለኛም ትልቅ ደስታን ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡