ኮሮናቫይረስ ፡ የአውሮፓ ህብረት መድኃኒት ተቆጣጣሪዎች ለአስትራዜኔካ ክትባት ፈቃድ ሰጡ

ታትሟል

የአውሮፓ ህብረት የመድኃኒት ተቆጣጣሪዎች ለአስትራዜኔካ የኮቪድ-19 ክትባት በህብረት አባላቱ አገራት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ሰጥተዋል።

በዚህም መሰረት ዕድሜያቸው 18ና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ይከተቡታል ማለት ነው።

ክትባቱ በአውሮፓ ህብረት አገራት ፈቃድ ቢያገኝም ክትባት አምራች ኩባንያው የገባውን ውል አፍርሷል በሚል ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።

ባለፈው ሳምንት በዩኬ የመድኃኒት አምራች የሆነው አስትራዜኔካ በአንደኛው አውሮፓ አገር ባጋጠመው የምርት ችግር ምክንያት በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ክትባቶችን ማቅረብ እንደማይችል ለአውሮፓ ህብረት አስታውቆ ነበር።

ለአውሮፓ አገር አባላት ቃል የተገባው የክትባት አቅርቦት መጠን በቂ ባለመሆኑ ውዝግብ ተነስቷል።

አስትራዜኔካ ለ27 የህብረቱ አባል አገራት ሊያቀርበው ከነበረው መጠን በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ነው ያቀረበው ተብሏል።

የአባላት አገሮቹን ወክሎ ክትባቶቹን እየገዛ ያለው የአውሮፓ ህብረት ክትባቶቹን እያከፋፈለ ካለበት መንገድ ጋር በተያያዘ ትችት እየቀረበበት ይገኛል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከኩባንያው ጋር የገባውን ውል ያተመ ሲሆን ውሉን አፍርሷል ለማለት እንደ ማሳያ አድርጎታል። ኩባንያው ውሉን ማክበር አለበት፣ ዩኬ ያላትን ክምትት ለህብረቱ አባላት ልታከፋፍል ይገባል በማለትም እየተከራከሩ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ አገራት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሰና ቮን ዴር ሌይን ለጀርመን ሬድዮ በዛሬው ዕለት በተናገሩት መሰረት በነሐሴ ወር ከክትባት አምራች ኩባንያ ጋር የተፈራረሙት ውል ፅኑ መሆኑን አስታውሰው ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት የኮቪድ-19 ክትባት ወጪ ንግድ ላይ ያሉ መመሪያዎችን እንደሚያጠብቅ አስጠንቅቋል።

የጤና ኮሚሽነሯ ስቴላ ካይራኪድስ እንዳሉት የአውሮፓ ህብረት "ዜጎቹን ለመጠበቅ ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃዎች ይወስዳል" ብለዋል።