ስመ ጥሩዋ ተዋናይት ሲሰሊ ታይሰን አረፈች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ፈር ቀዳጅ ከሚባሉት ስመ ጥር ተዋናይት መካከል የሆነችው ሲሰሊ ታይሰን በ96 አመቷ ማረፏን ስራ አስኪያጅዋ አስታውቋል። ሲሰሊ ህይወቷ ያለፈበት ምክንያት አልተጠቀሰም።
ተዋናይቷ ጠንካራ የሚባሉ የጥቁር አሜሪካውያንን ገፀ ባህርይ ወክላ በመጫወት ትታወቃለች። የሙያ ህይወቷ በፋሺን ሞዴልነት የጀመረችው ተዋናይት ለሰባት አስርት አመታት ያህልም በርካታ ፊልሞችን አበርክታለች።
ሲሰሊ በ1974 በነበረው የነፃነት እንቅስቃሴ ላይ በሚያጠነጥነውና ሚስ ጄን ፒትማን የህይወት ታሪክን ላይ ባተኮረው ፊልም ሁለት የኤሚ ሽልማቶችን አሸንፋለች።
ኢስት ሳይድ፣ ዌስት ሳይድ በሚለው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ዋነኛ ገፀ ባህርይ ሚና በመውሰድ በ1960ዎቹ የመጀመሪያ ጥቁር ሴት ተዋናይት ናት።
ከዚህም በተጨማሪ ከሶስት አመታት በፊት የክብር የኦስካር ሽልማትን በማሸነፍ እንዲሁ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ተዋናይት ናት።
በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የነፃነት ሜዳሊያን በሸለሟት ወቅት ከተዋናይነት ስኬቷ በተጨማሪ የታሪክን ሂደት የቀየረች በማለት አሞካሽተዋታል።
ሲሰሊ ጥቁር አሜሪካውያን ሴቶችን የሚያጠለሹ ገፀ ባህርያትን ውድቅ በማድረግ ትታወቃለች። የምትጫወታቸው ገፀ ባህርያት ጠንካራ፣ አዎንታዊ ይዘት ያላቸውንና እውነታውን የሚያንፀባርቁትን እንደሆነም በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
"ለአርባ አመታት ያህል ስራ አስኪያጇ ነበርኩ። እያንዳንዷ አመት ለኔ ትልቅ ፀጋና ክብር ነበር" በማለት ስራ አስኪያጇ ላሪ ቶምፕሰን የተዋናይቷን ሞት ባሳወቀበት በትናንትናው እለት ተናግሯል። በሰላም እንዳረፈች አክሎ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሲሰሊ የህይወት ታሪኳ ማስታወሻ 'አስ አይ አም' በሚል ርዕስ በዚህ ሳምንት የወጣ ሲሆን ቨልቸር የተባለው የኢንተርቴይንመንት መፅሄት ከማስታወሻው ውስጥ ሰባት ነጥረው የወጡ ታሪኮችን አትሟል።
የፕሬዚዳንት ኦባማ ረዳት ታላቅ የተባለውን ሽልማት አሸንፈሻል በማለት ስትደውልላት ስልኩን የዘጋችው አንዱ ነው።
"ኧረ ባክሽ! አልኩኝ እየሳቅኩኝ። በርግጠኝነት ሊቀልዱብኝ የደወሉ ነው የመሰለኝ። እናም ስልኬን እንዴት አገኘሽው? ምን አይነት የሞኝ ሰራ ነው እያልኩ ነበር። እሷ ግን እውነቴን ነው በማለት ልታሳምነኝ እየሞከረች ነበር" ብላለች።
ከዚህም በተጨማሪ የታዋቂው ጃዝ ሙዚቀኛ ማይልስ ዴቪስ ትራምፔት ተጫዋች የሆነውን ባለቤቷን በ1960ዎቹ እንዴት እንደተዋወቀችው ሰፍሯል። ሲሰሊ እንግዳ የሆነችበት ጎረቤቱ የነበረች ሴት ቤት ስኳር ሊቀበል በር በማንኳኳቱ ነው። በወቅቱ ያገለደመው ፎጣ ብቻ ነበር።
ተዋናይቷ በ17 አመቷ አንዲት ልጅ እንደወለደችና ከህዝብ እይታ ራቅ አድርጋ እንዳሳደገቻት ዩኤስኤ ቱደይ መፅሃፏን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ከዚህም በተጨማሪ የሙዚቀኛው ሌኒ ክራቪትዝ፣ የተዋናዮቹ ዴንዚል ዋሽንግተን ልጅ ካቲያና የታይለር ፔሪ ልጅ አማን ክርስትና እናት ናት።












