ሳኒ አባቻ ከናይጄሪያ ከዘረፉት ቢሊዮን ዶላሮች ምን ያህሉ ተመለሰ?

ታትሟል

የቀድሞ የናይጄሪያ ርዕሰ ብሔር ሳኒ አባቻ በቢሊዮን ዶላሮች ከአገራቸው ካዝና ዘርፈዋል። የዘረፉትን በልተው ሳይጨርሱ ግን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ከዚያ በኋላ ነው ይህን ቢሊዮን ዶላር የማስመለስ ዘመቻ ነው የተጀመረው፡፡ ለዐሥርታት ገንዘቡን ለማስመለስ ተደክሟል፡፡ ይህን ገንዘብ የማስመለሱን ሥራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ይሰራ የነበረው ሰው ለቢቢሲዋ ክሌር ስፔንሰር ታሪኩን አጫውቷታል፡፡

"ገንዘቡን ፈልገህ ማግኘት ትችላለህ?"

ርዕሰ ብሔሩ የዘረፉትን ዶላር እንዲፈልጉ ከተቀጠሩት መካከል የስዊዘርላንድ ዜጋ እና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ኤኔሪኮ ሞንፊሪኒ አንዱ ናቸው።

ሞንፊሪኒ እአአ 1999 ምሽት ላይ የደረሳቸው የስልክ ጥሪ የቀጣይ 20 ዓመታት ሕይወታቸውን ባላቀዱበት መንገድ እንዲመሩ እንደሚያስገድዳቸው አልጠረጠሩም ነበር።

"እኩለ ለሊት ላይ ደወለለኝ። አንድ ብርቱ ጉዳይ እንዳለው ነግሮኝ ጄኔቭ ከተማ ወዳረፈበት ሆቴል እንድመጣ ጠየቀኝ። 'መሽቷል ግን እሺ' አልኩት"

በስልኩ የወዲያኛው ጫፍ ያለው የወቅቱ የናይጄሪያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ድምጽ ነበር።

"ገንዘቡን ፈልገህ ማግኘት ትችላለህ?"

"የቱን ገንዘብ?"

"ሳኒ አባቻ የዘረፈውን፡፡"

ጠበቃ ኤኔሪኮ ሞንፊሪኒ እንደሚሉት በዚያ ሌሊት ያገኙት ባለሥልጣን ወደ ጄኔቭ የተላከው በናይጄሪያው ፕሬዝደንት ነበር፤ በወቅቱ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ደግሞ ኦሊ ሴንጎን ኦባሳንጆ ነበሩ።

ይህ ባለሥልጣን ጄኔቭ ድረስ የተጓዘው በሳኒ አባቻ የተዘረፈውን ዶላር ለማስመለስ ብቻ ነበር።

ሳኒ አባቻ ናይደጄሪያን ከ 1993 ህይወታቸው እስካለፈበት እንደ አውሮጳዊያኑ 1998 ድረስ ገዝተዋል። በሥልጣን ዘመናቸውም በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን ከምስኪን ሕዝባቸው ዘርፈዋል።

ጠበቃው ኤኔሪኮ ሞንፊሪኒ ቀደም ባለው የጥብቅና ሙያቸው በናይጄሪያውን ዘንድ መልካም ስም ገንብተዋል።

በቡና እና ካከዎ ምርት ላይ ለተሠማሩ በርካታ ናይጄሪያውን ጠበቃ ሆነው ወክለዋል።

ለዚህ ሥራም በናይጄሪያ መንግሥት የታጩት በእነዚህ ነጋዴዎች ምክረ ሐሳብ ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ።

"ገንዘቡን ማግኘት ትችላለህ? ገንዘቡን አግኝተህ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግስ ትችላለህ? ገንዘቡ ወደ ናይጄሪያ እንዲመለስ ማመቻቸት ትችላለህ?' በማለት ጠየቀኝ።

"አዎ' ስል መለስኩለት። ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ምን ያክል ጊዜ እንደሚያስፈልገኝ እርግጠኛ አልነበርኩም። ሁኔታውን በፍጥነት መረዳት ነበረብኝ" ይላሉ ጠበቃው።

ጠበቃው ሥራቸውን ሲጀምሩ የናይጄሪያ ፖሊስ ከሳኒ አባቻ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የተወሰኑ የተዘጉ የስዊዝ ባንክ ቁጥሮችን ሰጡት።

እነዚህ የባንክ አካውንቶች ሳኒ አባቻ እና ግብረ አበሮቹ የዘረፉትን ገንዘብ አስቀምጠውበት የነበረ የባንክ ቁጥር ስለመሆኑ ጠበቃው ሞንፍሪኒ ይገልጻሉ።

ሞንፍሪኒ ይህን ሥራቸውን በማስመልከት "ሪከቨሪንግ ስቶልን አሴትስ" (የተዘረፉ ንብረቶችን ማስመለስ) የሚል መጽሐፍ ጽፈዋል።

እንደ ጠበቃው ከሆነ የናይጄሪያ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ከጀመረ በኋላ እአአ 1998 ላይ ይፋ ባደረገው የመጀመሪያው ደረጃ ሪፖርት፤ የቀድሞ የናይጄሪያ ርዕሰ ብሔር እና ግብረ አበሮቻቸው 1.5 ቢሊዮን ዶላር መዝረፋቸውን አስታውቆ ነበር።

በዶላር የታጨቀ የጭነት መኪና

ጠበቃው በመጽሐፋቸው ላይ ናይጄሪያን የመዘበሩት ባለሥልጣናት የዘረፉትን ገንዘብ በጭነት መኪና ሁሉ ያንቀሳቅሱ እንደነበረ ጽፈዋል።

አባቻ አንድ አማካሪያቸውን ያስጠሩና ምንነቱ በግልጽ ለማይታወቅ የደኅንነት ጉዳይ ገንዘብ ወጪ እንዲያስተላልፍ ያዛሉ።

አማካሪውም የርዕሰ ብሔሩ ፊርማ ያረፈበትን ደብዳቤ በመያዝ ወደ አገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ያመራል።

ከማዕከላዊ ባንኩም የናይጄሪያ እና የተለያዩ አገራት ጥሬ ገንዘቦችን በጭነት መኪና ያጭቃል።" ከዚያም ገንዘቡ ወደ አባቻ ቤት ተወስዶ ይራገፋል" ይላሉ።

ሳኒ አባቻ እና ግብረ አበሮቹ ናይጄሪያን ከሚመዘብሩበት መንገዶች ይሄ አንዱ መሆኑን ጠበቃው በመጽሐፋቸው ገልጸዋል።

ሌላው የዘረፋ ዘዴያቸው እጅግን በተጋነነ ዋጋ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጄክቶችን ለወዳጆች በመስጠት ጉርሻ መቀበል ነው፡፡

እንዲሁም በናይጄሪያ መዋለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ከሚፈልጉ የውጪ አገራት ኩባንያዎች ለሥራ ማስኬጃ ጠቀም ያለ ዶላር መቀበል።

"ያገኘኋቸው የባንክ ዶሴዎች ከሌሎች የባንክ አካውንቶች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ፍንጭ ሰጥተውኝ ነበር" ይላሉ ጠበቃው ሞንፊሪኒ።

ሳኒ አባቻ ማን ነበሩ?

  • በናይጄሪያ የእርስ በእስር ጦርነት ጊዜ ከአገሪቱ ጦር ጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል።
  • በናይጄሪያ በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ቁልፍ ሰው ነበሩ። ከዚያም የአገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ።
  • እአአ 1993 ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆኑ።
  • መንግሥታቸው በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይወቀስ ነበር።
  • እአአ 1995 ላይ የአባቻ አስተዳደር 9 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ረሽኗል። በዚህም ከኮመንዌልዝ አገራት ናይጄሪያ ተሰርዛ ነበር።
  • የ10 ልጆች አባት የሆኑት አባቻ እአአ 1998 ዓ/ም ላይ በ54 ዓመታት ድንገት አረፉ፡፡

ይህን መረጃውን ይዘው ጉዳዩን ወደ ስዊዘርላንድ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይወስዱታል። ከዛም ያልጠበቁትን ውጤት አስመዘገቡ።

ጠበቃው ሞንፊሪኒ የአባቻ ቤተሰብ እና ግብረአበሮቹ ወንጀለኛ ቡድን ስለመፍጠራቸው ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነትን አገኘ።

ይህ መከራከሪያ ተቀባይነት ማግኘቱ ባለሥልጣናት የባንክ እንቅስቃሴዎችን እንዲመለከቱና እርምጃ እንዲወስዱ በር የሚከፍት ሆኖ ነበር።

የስዊዘርላንድ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ባንኮች በአባቻ ወይም በሌላ መጠሪያ የተከፈቱ የአባቻ የባንክ አካውንቶችን ይፋ እንዲያደርጉ አዘዘ።

በ48 ሰዓታት ውስጥ በስዊዘርላንድ ከሚገኙ ባንኮች እና የፋይናስ ተቋማት 95 በመቶ የሚሆኑት የአባቻ ቤተሰብ አካውንት ሊሆኑ የሚችሉ አካውንቶችን ይፋ አደረጉ።

"ይህ የሳኒ አባቻ ቤተሰብ በተቀረው ዓለምም በርካታ የባንክ አካውንቶች ሊኖረው እንደሚችል የሚጠቁም ነበር" ይላሉ ጠበቃው።

"የእያንዳንዱን አካውንት እንቅስቃሴ ስመለከት ገቢ የሚደረገው ገንዘብ ከየት እንደመጣ እንዲሁም ወጪ የሚደረገው የት እንደተላከ ማወቅ ቻልኩ። ወጪ እና ገቢው ወደ ሌሎች አገራት የሚላክ እና የሚገባ ገንዘብ መኖሩንም ያሳያል።" ይላሉ ጠበቃው።

ከጥቂት የባንክ አካወንት ተነስተው በተለያዩ አገራት ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚካሄድባቸው ብዛት ያላቸው አካውንቶችን መለየታቸውን ያስረዳሉ።

ለማንኛውም ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ገንዘብ ይላክ እንደነበረ ጠበቃው አረጋገጡ።

"ወደ በሃማስ፣ ኬይማን አይላንድ (የብሪታኒያ ግዛት) ጨምሮ ወደ ተለያዩ ሌሎች ስፍራዎች ገንዘብ በገፍ ሲላክ ነበር"

ጠበቃው ይህን ሥራ ለመከወን በተለያዩ አገራት ያሉ በርካታ የሒሳብ ሠራተኞችን ለመቅጠር መገደዳቸውን ይናገራሉ።

ጠቃው ሥራውን ከሰጣቸው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር የደረሱት ስምምነት ከሚያስመልሱት የገንዘብ መጠን 4 በመቶ ኮሚሽን በክፍያ መልክ እንደሚሰጣቸው ነው።

ሞፊሪኒ ግን የሥራውን ክብደት እና የወሰደባቸውን ጊዜ ከግምት በማስገባት "እንዲከፈለኝ የተስማመሁት በጣም አነስተኛ ገንዘብ ነው" ይላሉ።

የሳኒ አባቻ ቤተሰብ ገንዘቡን ወደ ናይጄሪያ እንዲመለስ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ፈተና ሆነው እንደነበረ ይናገራሉ።

"እያንዳንዱ ምርመራችን እንዲቋረጥ ማመልከቻቸውን በየፍርድ ቤቱ ሲያቀርቡ ነበር"

ሌላው የተዘረፈውን ገንዘብ ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት እንቅፋት የነበሩት የስዊዘርላንድ ፖለቲከኞች ነበሩ።

ፖለቲከኞቹ የተዘረፈው ገንዘብ ወደ ናይጄሪያ እንዲመለስ ብንፈቅድ ዳግም ላለመዘረፉ ምን ማረጋገጫ አለን ብለው መከራከሪያ ያቀርቡ ነበር።

ጠበቃው ሞንፊሪኒ በሳኒ አባቻ ቤተሰብ በተለያዩ የስዊዝ ባንኮች ተቀምጦ ከነበረ ገንዘብ 508 ሚሊዮን ዶላር ከ2005 እስከ 2007 (እአአ) ባሉት ዓመታት ወደ ናይጄሪያ ተመላሽ መደረጉን ይናገራሉ።

እአአ 2018 ላይ ደግሞ ስዊዘርላንድ ለናይጄሪያ የመለሰችው ገንዘብ መጠን 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ ነበር።

ሌሎች አገራት ግን እንደ ስዊዘርላንድ በፍጥነት ገንዘቡን ለመመለስ ቁርጠኝነት አልነበራቸውም።

"ለምሳሌ በሌችተንስታይን (አውሮፓዊት አገር) ከፍተኛ ችግር ነበር። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሌችተንስታይን 277 ሚሊዮን ዶላር ለናይጄሪያ ልካለች።

ቻናል አይላንድ ኦፍ ጄርሲ ደግሞ 2020 ላይ 308 ሚሊዮን ዶላር ልካለች"

ጠበቃው እንደሚሉት ሌችተንስታይን እና ቻናል አይላንድ ኦፍ ጄርሲ የተዘረፈውን ገንዘብ ለናይጄሪያ ለመመለስ የተስማሙት ተመላሽ በሚደረገው ገንዘብ የናይጄሪያ መንግሥት ድልድዮችን እና መንገድ እንደሚገነባበት ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነበር።

አሁን በአባቻ የተዘረፈውን ገንዘብ ያልመለሱ አገራት አሉ። 6 አገራት።

ጠበቃው 30 ሚሊዮን ዶላር በዩናይትድ ኪንገደም፣ 144 ሚሊዮን ዶላር በፈረንሳይ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

እስካሁን ግን ጠበቃው 2.4 ሚሊዮን ዶላር ለናይጄሪያ ማስመለሳቸው ገልፀዋል።

"ሥራውን ስጀምር ሰዎች ሳኒ አባቻ የዘረፈው ገንዘብ ከ4-5 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ሲናገሩ ነበር። ይህን ማመን አልችልም። የሆነው ሆኖ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ማስመለስ ችለናል" ይላሉ፡፡

ጠበቃው ባላቸው መረጃ መሠረት አሁን ላይ የአባቻ ቤተሰቦች እንደ ከዚህ ቀደሙ የቅንጡ ሕይወት እየመሩ አይደለም።

ጠበቃው ሥራቸውን መለስ ብለው ሲመለከቱ እርካታ ይሰማቸዋል።

"ለልጆቼ የተዘረፈውን ገንዘብ ፈልጌ እንዳገኘሁ፣ እንዳይንቀሳቀስ ስለማድረጌ እና መንግሥታት ገንዘቡን ለሚገባቸው ናይጄሪያውን እንዲመለሱ ማስገደዴን በኩራት እነግራቸዋለሁ"

"ሥራውን ፈጽመናል"

አባሪ መረጃ

በታሪክ ውስጥ ሌሎች የአገር መሪዎችም እንደ ሳኒ አባቻ ከአገራቸው ቢሊዮኖችን ዘርፈዋል፤ ከነዚህ መካከል፡፡

  • ሞሐመድ ሱሃርቶ ከእአአ 1967-98 የኢንዶኔዢያ ፕሬዝደንት የነበሩ ከ15-35 ቢሊዮን ዶላር የዘረፉ
  • ፈርዲናንድ ማርኮስ ከእአአ 1972-86 የፊሊፒንስ ፕሬዝደንት የነበሩ፤ ከ5-10 ቢሊየን ዶላር የመዘበሩ
  • ማቡቶ ሴሴ ሴኮ ከእአአ 1965-97 የዛዬር (የዛሬዋ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ) ፕሬዝደንት የነበሩ እና 5 ቢሊየን ዶላር የዘረፉ