ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ክትባት ለመከተብ አጭበርብረዋል የተባሉ ኃላፊ ከስራቸው ለቀቁ
ከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የካዚኖ ቁማር ኩባንያ የሚመሩት ዋና ስራ አስፈፃሚ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት አጭብርብረዋል መባሉን ተከትሎ ከስራቸው ለቀቁ።
ኃላፈውና ባለቤታቸው ባለስልጣናቱን አታለዋል በሚል ተከሰዋል።
ግሬት ካናዲያን ጌሚንግ የተባለ የካዚኖ ቁማር ድርጅት የሚመሩት ሮድ ቤከርና ባለቤታቸው ኢካትሪና ገጠራማ ወደሆነው ዩኮን ግዛት ክትባት ለመከተብ አቅንተው ነበር።
ግዛቱ የቀደምት ካናዳውያን መኖሪያ ሲሆን ከሌሎች የካናዳ ክፍሎች በበለጠ ፈጣን የሆነ የክትባት አሰጣጥ ስርአት እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ።
ባለትዳሮቹ ወደ ቦታው ሲያመሩም የሆቴል ሰራተኞች ነን በሚል ሽፋን ነው።
በባለፈው ሳምንት በግዛቲቱ ውስጥ በምትገኝ ቢቨር ክሪክ በምትባል መንደር ውስጥ ተከትበው ከጨረሱ በኋላ ወደ አየር ማረፊያ ውሰዱን ማለታቸውን ተከትሎ ነው የተጋለጡት።
" በዚህ ራስ ወዳድ በሆነ ባህርያቸው በጣም ተበሳጭቻለሁ" በማለት የዩኮን ማህበረሰብ አገልግሎት ሚኒስትር ጆን ስትሬይከር ተናግረዋል።
"በዚህ መንገድ ሰው አጭበርብሮ እንዲህ አይነት ተግባር ይፈፅማል የሚል ነገር በጭራሽ አላሰብንም" ብለዋል አክለውም።
ከዚሁ ጋር ተያያይዞ የዋይት ሪቨር ፈርስት ኔሽን፣ የአካባቢው የቀደምት ህዝቦች ኃላፊ አንጄላ ዴሚት በበኩላቸው "የእድሜ ባለፀጎቻችንና ተጋላጭ ማህበረሰቦቻችንን ስጋት ውስጥ የሚከቱ የአንዳንድ ግለሰቦች ድርጊት በጣም አሳስቦናል። ተራን ባለመጠበቅ እንዲህ አይነት አስነዋሪ ስራ መፈፀም ራስ ወዳድነት ነው" ብለዋል።
ሮድ ቤከርና ባለቤታቸው ከቫንኮቨር ግዛት ወደ ዩኮን በሄዱበት ወቅት አስገዳጅ የሆነውን የ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ ባለማክበር ተቀጥተዋል።