በኔዘርላንድስ 'በ40 ዓመታት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ' ተቃውሞ 3ኛ ቀኑን ይዟል

የኔዘርላንድስ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

በኔዘርላንድ መንግሥት ወረርሽኙን ተከትሎ በወሰደው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ የተቆጡ ዜጎች አደባባይ ወጥተዋል።

ካለፈው ቅዳሜ የጀመረው ተቃውሞ በርካታ ከተሞችን ያዳረሰ ሲሆን ፖሊስ እንደሚለው እስከ አሁን በነበረው ተቃውሞ 150 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በሮተርዳም ከተማ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል።

የሮተርዳም ከንቲባ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ያስተላለፉት ጥብቅ መመርያ ቸል ተብሎ ነው ተቃውሞ የቀጠለው።

ይህ ረብሻ የተቀሰቀሰው ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን ወረርሽኙን ለማቆም አዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ያበሳጨቸው ዜጎች ናቸው 'አሁንስ በዛ!' ብለው አደባባይ የወጡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ ተቃዋሚዎቹን በጠንካራ ቃላት አውግዘዋል።

ኔዘርላንድስ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በተህዋሲው የተያዙባት አገር ስትሆን የሞቱባት ዜጎች ግን 13ሺ 500 ብቻ ናቸው።

ትናንት ሰኞ አብዛኛዎቹ የኔዘርላንድስ ከተሞች ውስጥ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር የተጋጩ ሲሆን ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በተለይ በአምስተርዳም፣ በሮተርዳም፣ በአመርስፎርት እና በጊሊየን ከተሞች ከበድ ያለ ተቃውሞዎችን ለማብረድ ታትሯል።

በሄግ ከተማ በመንገድ ላይ ተቃዋሚዎች እሳት ያነደዱ ሲሆን ፖሊስ በብስኬሌት መጥቶ ጥቂት ተቃዋሚዎችን ለመበተን ሲሞክር ግን ግጭት መቀስቀሱን እና ተቃዋሚዎች ድንጋይ መወርወር መጀመራችን የቢቢሲ ወኪል አና ሆሊጋን ከሄግ ዘግባለች።

በዋና ከተማዋ አምስተርዳም በርካታ ንብረቶች መውደማቸውን ተከትሎ ፖሊስ በርካቶችን ማሰር ጀምሯል።

በሮተርዳም ፖሊስ አስለቃሽ ጭስና ግፊት ያለው ውሀ በመርጨት ተቃውሞን ለመደምሰስ ቢሞክርም አልተሳካለትም።

የሮተርዳም ከንቲባ ፖሊስ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ የሚያስችለውን የአስቸኳይ ጊዜ ሰነድ ፈርመዋል።

ከትናንት በስቲያ እሑድ የነበረውን ረብሻ የደች ፖሊስ 'በ40 አመታት ውስጥ ከታዩት ሁሉ የከፋ' ብሎታል።

እስከአሁን ፖሊስ 250 ዜጎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

የኮቪድ መመርመርያ ማዕከል የነበረ በሰሜን ኔዘርላንድ የሚገኝ ቦታን ተቃዋሚዎች እሳት ለኩሰው አንድደውታል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰልፈኞቹን እነዚህ ውንብድና ላይ ያሉ እንጂ ሰላማዊ ሰልፈⶉች አይደሉም ሲሉ አውግዘዋቸዋል።

'እነዚህን ምን አደባባይ እንዳስወጣቸው አናውቅም። ተቃውሞ አይደለም። ይህ የወንጀል ተግባር ነው፤ እርምጃውም ያንን መሰረት ያደርጋል' ብለለዋል ጠለቅላይ ሚኒስትሩ።

የደች መንግሥት ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ጠንካራ የሚባለውን ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።

በዚህ ገደብ መሠረት ማታ ከ3 ሰዓት በኋላ እስከ ንጋት 10 ተኩል ድረስ መንቀሳቀስ አይቻልም።

ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ኔዘርላንድስ እንዲህ ዓይነት ጥብቅ ሰዓት እላፊ ጥላ አታውቅም።

ይህን ገደብ የሚጥስ ማንኛውም ዜጋ 84 ዩሮ ይቀጣል።

ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ ሬስቶራንቶችና ቡና ቤቶች ዝግ ሆነዋል፥ ካለፈው ወር ጀምሮ ደግሞ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ለኑሮ እጅግ ወሳኝ የማይባሉ ሱቆች እንዲዘጉ ተደርገዋል።

ከብሪታኒያ፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከደቡብ አሜሪካ ወደ ኔዘርላንድስ በረራዎችም ዝግ ሆነዋል።