ኮሮናቫይረስ፡ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸውን ሊለቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ዛሬ ማክሰኞ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ይለቃሉ።
ኮንቴ ሥልጣናቸውን የሚለቁት ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በተከሰተው ምስቅልቅል ያሳዩት አስተዳደር ደካማ ነው በሚል ከተተቹ በኋላ ነው።
በጣሊያን 85ሺ ሰዎች በተህዋሲው መሞታቸው ይታወሳል።
ኮንቴ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ በአገሪቱ ፕሬዝዳንቱ ሌላ አዲስ ጠንካራ መንግሥት እንዲመሠርቱ ዕድሉ ይሰጠኛል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
በፕሬዝዳንቱ ይህ ዕድል ሲሰጣቸው ምክር ቤት ከገቡ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግረው አዲስ ጠንካራ ጥምረት ያለው መንግሥት መሥርተው ወደ ሥልጣን ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጁሴፔ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን መንግሥት የመመሥረቱን ኃላፊነት ፕሬዝዳንቱ ለሌላ ሰው አሳልፈው ይሰጣሉ።
ጁሴፔ በጣሊያን ምክር ቤት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብረውና ጠንካራ ጥምረት ፈጥረው መንግሥት ማቆም ካልቻሉ ግን አዲስ አገር አቀፍ ምርጫ ሊጠራ ይችላል።
በደንቡ መሠረት ዛሬ ኮንቴ ሚኒስትሮቻቸውን ሰብስበው ሥልጣን የመልቀቅ ሐሳብ እንዳላቸው በይፋ ይናገሩና ይህንኑ ያደርጋሉ፤ ከዚያ ፕሬዝዳንት ሰርጌዮ ማቴሬላ ጋር ሄደው ይህንኑ ያሳውቃሉ።
ኮንቴ ከ2018 ጀምሮ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነቀፌታ በርትቶባቸው በታችኛው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የመተማመኛ ድምጽ ተሰጥቶባቸው ነበር።
በሥልጣን የሚያስቀጥለውን መተማመኛ ድምጽ ማግኘት ችለዋል።
ይህ የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥባቸው የሆነው የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ የሚመሩትና ትንሹ 'ኢታሊያን ቪቫ' ፓርቲ ከኮንቴ መንግሥት ጥምረት ራሱን በማውጣቱ ነው።
ማቲዮ ሬንዚ ፓርቲዬ ወደ ጥምር መንግሥቱ የሚመለሰው እኔ ያቀረብኳቸው ቅድም ሁኔታዎችን ለመቀበል ሲችል ብቻ ነው ብለዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ አንዱ ከኮንቴ ጋር ያላስማማቸው ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረት ማገገምያ ፈንድ ብሎ ለጣሊያን የሰጠውን 254 ቢሊዮን ዶላር ለምን ጉዳይ ይዋል የሚለው ነው።
ጥቁርና መጤ ጠል የሚባለው ፋይቭ ስታር ሞቭመንት ፓርቲ ከኮንቴ ጎን እንደሚሆን ይፋ አድርጓል።
ገለልተኛኛ ከፖለቲከኛ ይልቅ ሙያተኛ ናቸው የሚባሉት ኮንቴ ተከታታይ ሁለት የመንግሥት አስተዳደሮችን መርተዋል።
ለ15 ወራት ያህል ኤም5ኤስ የተባለው ፓርቲና ቀኝ አክራሪው የማቲዯ ሳልቪኒ ፓርቲ የመሰረቱትን ጥምረት መርቷል።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ኤም5ኤስ እና ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች የመሰረቱትም የጥምር መንግሥት ለመምራት ችለዋል።
በጣሊያን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አዲስ አገር አቀፍ ምርጫ ማድረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ጆሴፔ ኮንቴ አዲስ ጠንካራ የጥምር መንግሥት መሥርተው ወደ ሥልጣናቸው ይመለሳሉ የሚል ትልቅ ተስፋ አለ።












