ጉግል በአውስትራሊያ አገልግሎቱን እንደሚያቋርጥ አስጠነቀቀ

ታትሟል

ጉግል መረጃ ማሰሻውን (ሰርች ኢንጂን) ከአውስትራሊያ እንደሚያወጣ አስጠነቀቀ።

ጉግል ይህን ያለው አውስትራሊያ ጉግል፣ ፌስቡክና ሌሎችም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ለሚዲያ ተቋማት ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ሕግ ማርቀቋን ተከትሎ ነው።

ጉግል፣ ፌስቡክ ወይም ሌሎች የሚዲያ ተቋሞች ዜና ከመለጠፋቸው በፊት የዘገባው ባለቤት ለሆኑ መገናኛ ብዙኃን ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚያዝ ሕግ ነው አውስትራሊያ ያወጣችው።

ይህን መሰል ሕግ ሲወጣ የአውስትራሊያ የመጀመሪያው ነው። ሕጉን የተቃወሙት የቴክኖሎጂ ተቋሞች አገልግሎታቸውን እንደሚያቋርጡ አስታውቀዋል።

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን ሕግ አውጪዎች ለማስፈራሪያ አይንበረከኩም ብለዋል።

የአውስትራሊያ ሕግ፤ መንግሥታት በምን መንገድ የቴክኖሎጂ ተቋሞችን ይቋቋማሉ የሚለውን ለውይይት ክፍት ያደረገ ነው።

ሕጉ ጉግልና ፌስቡክ ከሚዲያዎች ጋር ለዘገባ ስለሚሰጥ ክፍያ እንዲደራደሩ ይደነግጋል።

የጉግል የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሜል ሲልቫ "ሕጉ አይሠራም። አውስትራሊያን ጥሎ ከመውጣት ውጪ አማራጭ የለንም" ብለዋል።

ሕግ አውጪዎች በበኩላቸው ጉግል አውስትራሊያ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከረ ነው ብለው ይከራከራሉ።

የሕዝብ እንደራሴው ሬክስ ፓትሪክ "እንደዚህ አይነት ደንብ በመላው ዓለም ሲወጣ ከእያንዳንዱ አገር ገበያ ሊወጡ ነው?" ሲሉ ተቃውሞ አሰምተዋል።

አውስትራሊያ ውስጥ ግንባር ቀደሙ መረጃ ማሰሻ ጉግል ነው። ገበያው ላይ ሌላ ጠንካራ ተወዳዳሪ የለውም።

ሕግ አውጪዎች እንደሚሉት፤ ጉግል ደንበኞቹን የሚያገኘው ዜና ለማንበብ ወደ ማሰሻው ከሚሄዱ ሰዎች ስለሆነ መገናኛ ብዙኃን የድርሻቸውን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው።

ጉግል የሚፈጽመው ክፍያ ለሚዲያዎች ድጋፍ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

እአአ ከ2005 ወዲህ የሕትመት ሚዲያ የማስታወቂያ ገቢ 75 በመቶ ቀንሷል።

አውስትራሊያ ውስጥ በጉግል አማካይነት ከሚሰራጨው መረጃ 12.5% ዜና ነው።

ጉግል አገልግሎቱን ለማቋረጥ ማስፈራራቱ አዲሱ ሕግ ምን ያህል እንዳሳሰበው ይጠቁማል።

በመላው ዓለም ካሉ የመረጃ ማሰሻዎች መካከል ጉግል 90 በመቶ ገበያውን ይሸፍናል። አብዛኛውን ገቢ የሚያገኘው ከማስታወቂያ ነው።

በወረርሽኙ ሳቢያ መገናኛ ብዙኃን ገቢያቸው ሲያሽቆለቁል፤ ጉግል ግን ገቢው ንሯል።

ጋዜጠኝነትን ማበረታታት እንደሚፈልግ ጉግል ቢገልጽም፤ አውስትራሊያ ውስጥ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ይህንን አያንጸባርቅም።

አንዳንድ አውስትራሊያውያን በአገራቸው ውሳኔ ደስተኛ ሲሆኑ፤ ጉግል ከሌለ በምን መንገድ መረጃ እናገኛለን ሲሉ የሚጠይቁም አሉ።

ጉግል አገልግሎቱን ሲያቋርጥ ጂሜል፣ ጉግል ማፕና ሌሎችንም የጉግል ክፍሎች ማግኘት አለመቻላቸው ያሳሰባቸውም አሉ።