ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ባይደን በኮቪድ-19 የሚሞቱ አሜሪካዊያን ቁጥር በቅርቡ ግማሽ ሚሊዮን ይደርሳል አሉ
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቃል በገቡት መሠረት የኮቪድ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር አዲስ ዘመቻ በይፋ ጀምረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዘመቻውን የጀመሩት "ልክ በጦርነት ጊዜ ውስጥ የሚኖራቸውን የሕግ ሥልጣን አግባብ" ተጠቅመው አዳዲስ ፍጹማዊ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በመስጠት ነው።
ይህ አሰራር ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ፣ የክትባትና ሌሎች ግብአቶችን በፍጥነት ለማምረት፣ አዳዲስ አስገዳጅ ደንቦችን በፌዴራል ደረጃ ለማውጣት የሚያስችላቸው ነው።
በዚህም መሠረት ክትባት መስጠቱ እንዲሳለጥ፣ ሰዎች በፍጥነትና በቀላሉ እንዲመረመሩ ለማስቻል አዲስ አሰራር ተጀምሯል ብለዋል ባይደን።
አዲሱ የአስቸኳይ ጊዜ ደንብ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ እንደ ጭንብል ያሉ ግብአቶች ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጥፍ እንዲመረቱ ያስችላል።
ባይደን በዚህ አዲስ ዘመቻ 10 አዳዲስ መመርያዎችን ፈርመዋል።
"ኮቪድን ለማሸነፍ ወራት ሊወስድ ይችላል ሆኖም አሜሪካዊያን አብረን ከተጋገዝን ድል እናደርገዋለን" ብለዋል ባይደን።
ጆሴፍ ባይደን ይህን እርምጃ እየወሰዱ ያሉት 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ በፈጸሙ በቀጣዩ ቀን ነው።
ይህ የባይደን አዲሱ ውሳኔ ከትራምፕ የሚለየው ፌዴራላዊና ማዕከላዊ ውሳኔ በመሆኑ ሲሆን፤ ትራምፕ በኮቪድ ጉዳዮች ላይ ይከተሉ የነበረው አሰራር ግን ግዛቶች የራሳቸውን ውሳኔ በራሳቸው እንዲወስኑና እንዲከተሉ በመተው ነበር።
ባይደን ይህ በአገር የመጣ ጠላት ስለሆነ በአንድ ነው መንቀሳቀስ ያለብን ይላሉ።
አሜሪካ አሁን በተህዋሲው የሞቱባት ዜጎች 400ሺህ ያለፈ ሲሆን 24 ሚሊዮን ሕዝቦች ደግሞ ተህዋሲው ይዟቸው ይገኛሉ።
ይህ ዘመቻ ቀላል አይሆንም ያሉት ባይደን ነገሮች ሊሻሻሉ ሲሉ እየከፉ ነው የሚመጡት፤ በሚቀጥለው ወር የሟች አሜሪካዊያን ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ብለዋል።
በዚህ ተህዋሲ ምክንያት በ2ኛው የዓለም ጦርነት በመላው ዓለም ከሞቱ ሰዎች ቁጥር የበለጠ አሜሪካዊያንን አጥተናል ብለዋል።
ባይደን በመጀመርያዎቹ መቶ ቀናት ውስጥ 100 ሚሊዮን ጠብታዎችን ለማድረስ ቃል ገብተዋል።
ባይደን ይህን ባሉበት ወቅት አንድ ጋዜጠኛ ይህ ቁጥር ራሱ በቂ አይደለም ብሎ ሲሞግታቸው ቆጣ ብለው፥ "ተው እንጂ! ይሄን ቁጥር ይፋ ሳደርግ በተግባር የሚውል ሊሆን አይችሉም ስትሉ አልነበረም እንዴ?" ሲሉ መልሰዋል።
ባይደን እንደ ትራምፕ በሳይንቲስቶች ሥራ ጣልቃ አልገባም ያሉ ሲሆን የጤና አማካሪዎቻቸው ነጻ ሆነው ሳይንሳዊ ውሳኔ እንዲወስኑ እንደሚያስችሏቸው ተናግረዋል።
ከፍተኛ አማካሪ አንቶኒ ፋውቺ በበኩላቸው ይህ ፕሮግራም የነበረ ሲሆን ባይደን እያደረጉ ያሉት ሁኔታዎችን ማሳለጥ ነው ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደታሰበው ከ70 እስከ 85 ከመቶ አሜሪካዊ ከተከተበ ወደ ጤናማው ዘመን የመመለስ እደል አለን ብለዋል ፋውቺ።
ፋውቺ ትልቁ ፈተና ብለው የሚያስቡት ክትባቱ ላይ እምነት የሌለላቸውን አሜሪካዊያንን እንዴት ማሳመን ይቻላል የሚለው ነው።
አሁን በባይደን ውሳኔ መድኃኒት አምራቾች በከፍተኛ ሁኔታ የክትባት ምርት እንዲያዘጋጁ ይደረጋል። ከወዲህ አንዳንድ ግዛቶች ክትባት አነሰን እያሉ ይገኛሉ።
እስከአሁን ባለው 16 ሚሊዮን ሰዎች ክትባት አግኝተዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ኮቪድን ለመከላከል ሁሉን አቀፍና ግልጽ አቅጣጫ የለውም ተብሎ ሲተች ነበር።
በዚህ አዲሱ የባይደን ዘመቻ በቀጣይ መቶ ቀናት ትምህርት ቤቶች ቀስ በቀስ እንዲከፈቱ ይደረጋል።
በስታዲየሞችና ትልልቅ የማኅበረሰብ ማዕከላት የክትባት መስጫዎች ሆነው ያገለግላሉ።
ከዘመቻው ጋር በተያያዘ ላሉ ወጪዎች የምጣኔ ሀብት ማነቃቂያ ተብሎ ከተያዘው 2 ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተቀናሽ የሚሆነው ነው።
ዓለም አቀፍ ተጓዦች ወደ አሜሪካ ለመግባት ከኮቪድ ነጻ ስለመሆናቸው ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ከዚያም ደግሞ ራሳቸውን ለ14 ቀናት መወሸብ ይገደዳሉ።
ጭምብል ማጥለቅና ርቀት መጠበቅ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አየር መንገዶች፥ ባቡሮችና አውቶቡሶች ውስጥ ግዴታ ይደረጋል።
ከትራምፕ በተለይ በባይደን አዲዙ የዘመቻ እቅድ አሜሪካ የኮቫክስ ፕሮጀግትን ትቀላቀላለች። ይህ ፕሮጀክት ለድሀ አገራት ክትባቱን ለማድረስ የሚተጋ ነው።
ባይደን ትራምፕ ያቋረጡትን ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር አብሮ መሥራትንና በገንዘብ መደገፍን እንደሚቀጥሉ አብስረዋል።