የቺፕ እጥረት የመኪና-ኩባንያዎችን ምርትን እያስተጓጎለ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውዲ "በቀውስ ላይ ቀውስ " ብሎ በጠራው የኮምፒውተር-ቺፕ እጥረት ምክንያት ምርቱ መዘግየት ገጥሞታል።
ኃላፊው ማርከስ ዱስማን በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ10,000 ያነሱ መኪኖችን ለማምረት እንዳቀደና ከ10,000 በላይ ሠራተኞቹን ደግሞ በአስገዳጅ ሁኔታ እረፍት ሊያስወጣ ወስኗል።
እንደ እናት ኩባንያው ቮልስዋገንም ሆነ ተፎካካሪው ሆንዳ ባለፈው ሳምንት በቺፕስ እጥረት ምክንያት የምርት መዘግየት እንደገጠማቸው አሳውቀዋል።
ዱስማን ለፋይናንሻል ታይምስ እንደገለጹት መኪና አምራቾች በሁኔታው እጅጉን ተገርመዋል።
ቺፕ በዘመናዊ መገልገያዎች ውስጥ የሚገኝ ወሳኝ እቃ ሲሆን በኮምፒውተር፣ በሞባይል ስልኮችና በሌሎችም ቁሶች ውስጥ ይገኛል። ቺፕ የመገልገያዎች ኤሌክትሪካዊ የትስስር ክፍል ሲሆን በአንድ መገልገያ ውስጥ ያለ አጠቃላይ ሥርዓት ለማዋሃድና ለመቆታጠር ጠቃሚ ነው።
"ውስን ምርት"
በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 የአዲስ መኪና ሽያጭ ደካማ መሆኑን ተከትሎ አምራቾች ለኮምፒውተር ቺፕስ አምራች የቻይና ፋብሪካዎች የሰጡትን ትዕዛዝ አቋርጠዋል።
በዓመቱ መጨረሻ ላይ ግን "ሁሉም ሰው በገበያው መነቃቃት በጣም ተገረመ" ሲሉ ዱስማን ተናግረዋል።
ሆኖም አዲስ ቺፕስ ማዘዝ ቀላል አልሆነም።
የሲሲኤስ ኢንሳይት ተንታኝ ጂኦፍ ብሌበር "ሴሚኮንዳክተሮች ሰፋ ያሉ መተግበሪያዎች ቢኖራቸውም ሲሊኮንን ማምረት የሚችሉ ኩባንያዎች በጣም ውስን ናቸው" ብለዋል።
"ፍላጎቱ ከፍተኛ ቢሆንም አቅርቦቱም አነስተኛ ሲሆን ማንኛውም ድንገተኛ ፍላጎቶችን ማስተናገድ በጣም አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ" ሲሉ ገልጸዋል።
"ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ከመረጃ ሥርዓት እስከ ካሜራ፣ እንደራዳር እና ርቀት መለኪያ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ የተትረፈረፈ ሲሊኮን ያስፈልጋል" ብለዋል።
የመኪና አምራቾች ፍላጎት "ከስማርት ስልኮች እና ከሌሎች አምራቾች ፍላጎት ጋር ይወዳደራል" ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ኮምፒውተሮች እና ጌም ላሉ መሣሪያዎች በገበያው ውስጥ ያላቸው ፍላጎት መጨመር ትዕዛዝ ለማቅረብ አስቸጋሪ አድርጎታል።
እጥረቶቹ የመርሴዲስ አምራች የሆነውን ዴይምለርን ጨምሮ ፊያት፣ ፎርድ፣ ሆንዳ፣ ኒሳን ፣ ሱባሩ እና ቶዮታ ለቀናትም ሆነ ለሳምንታት ምርታቸውን እንዲያቆሙ አስገድዷል።












