ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ አፍሪካ የየብስ ድንበሮቿን ዘጋች
ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመግታት የየብስ ድንበሮቿን እስከ አውሮፓውያኑ የካቲት 15 ድረስ መዝጋቷን የአገሪቷ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ አስታወቁ።
ፕሬዚደንቱ ሰኞ ዕለት በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ፤ በአገሪቷ ያለው የወረርሽኙ ስርጭት አስደንጋጭ ነው ብለዋል። በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም በመጀመሪያው ዙር ወረርሽኝ ወቅት ከታየው የወረርሽኙ ጣሪያ የበለጠ መሆኑን ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ እንዳሉት ከአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ወዲህ ማለትም በ12 ቀናት ውስጥ ብቻ 190 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ15 ሺህ በላይ ሰዎችም ሆስፒታል ይገኛሉ።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የክዋዙሉ ናታል ግዛት ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እያስተናገደች ነው።
ይሁን እንጂ ፕሬዚደንቱ በጋውቴንግ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን በመግለፅ፤ በዓል ለማክበር ወደተለያየ ቦታ የሄዱት ሲመለሱ ቁጥሩ እንደሚጨምር ይጠበቃል ብለዋል።
በዚህም ሳቢያ ባሳለፍነው ታኅሳስ በአገሪቷ ተጥለው የነበሩ ገደቦች ይራዘማሉ ተብሏል።
በአልኮል ሽያጭ ላይ የተጣለው ገደብ ተግባራዊ መሆኑ ይቀጥላል። የወረርሽኙ ማዕከል በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ የባህር ዳርቻዎች ፣ መናፈሻዎች ዝግ ሆነው ይቆያሉ።
የቀብር ሥነ ሥርዓት የወረርሽኙን ሥርጭት የሚያስፋፋ ሁነት ሆኖ መቀጠሉንም ፕሬዚደንቱ አስጠነቅቀዋል።
ፕሬዚደንቱ " የቀብር ሥነ ሥርዓት ለበርካታ ሰዎች የሞት ወጥመድ ሆኗል" ሲሉም ሰዎች ቤታቸው እንዲቆዩ አሳስበዋል።
ደቡብ አፍሪካ ልታካሂደው ያቀደችው የክትባት መርሃ ግብር በተመለከተም ፕሬዚደንቱ መርሃ ግብሩ አገሪቷ በታሪኳ የምታስተናግደውና እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው የሎጂስቲክ ፕሮጀክት ይሆናል ብለዋል።
በሚቀጥሉት ወራቶች የሚደርስ 20 ሚሊየን ዶዝ [መጠን] ክትባት ማግኘቷን የተናገሩት ፕሬዚደንቱ፤ ከተለያዩ ክትባት አምራቾች ጋርም ድርድር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።