ኮሮናቫይረስ ፡ በእንግሊዝ ለበርካታ ሕዝብ የኮቢድ-19 ክትባት የሚሰጡ ማዕከላት ሊከፈቱ ነው

ታትሟል

እንግሊዝ በመላው አገሪቱ በሰባት ቦታዎች ላይ በሚቋቋሙ የኮሮናቫይረስ የክትባት መስጫ ማዕከላት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ልትከትብ መሆኑን አስታወቀች።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት በዚህ ሳምንት ተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትንም ይከፈታል ተብሏል።

መንግሥት በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ እድሜያቸው ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ፣ የጤና ሠራተኞች እንዲሁም ተያያዥ የጤና ችግር ያለባቸውን በመላዋ ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ 15 ሚሊዮን ሰዎችን ያህል ሰዎች ለመከተብ እቅድ ይዟል።

የጤና ሚኒስትሩ ማት ሐንኮክ የመንግሥትን የክትባት አሰጣጥ እቅድ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ሚኒስትሩ "ይህ ምክረ ሃሳብ ከወረርሽኙ ለመውጣት የመሰረት ድንጋይ የምንጥልበት ነው" ብለዋል።

መንግሥት በየቀኑ ለምን ያህል ሰዎች ክትባቱን እንደሰጠ የሚያሳይ አሃዛዊ መረጃም ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሃንኮክ እሁድ እለት እንዳሉት በዩናይትድ ኪንግደም 2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ተከትበዋል። በእንግሊዝ በየቀኑ ወደ 200 ሺህ ያህል ክትባቶች መስጠት ተችሏል።

ዩናይትድ ኪንግደም ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ 80 ሺህ ያህል ሰዎችን በተህዋሲው ምክንያት አጥታለች።

በአገሪቱ ከፍተኛ በተህዋሲው የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት ከተማ ሱሬይ ስትሆን፣ በከተማዋ ጊዜያዊ የቀብር ማስፈፀሚያ ቢሮ በሆስፒታል ውስጥ እንዲከፈት ተደርጓል።

ይህ የሆነው የቀብር አስፈጻሚዎች ከአቅማቸው በላይ የሆነ አስከሬኖችን መቀበላቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

ቢያንስ 200 አስከሬኖች ከዚህ ቀደም የጦር ኃይሉ ሆስፒታል በነበረበት ስፍራ በጊዜያዊነት የተቀመጡ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ጊዜያዊ ማቆያ በቅርቡ እንደሚከፈት የአካባቢው አስተዳደር ለቢቢሲ ገልጿል።

ቅዳሜ እለት ሳይንቲስቶች እጅግ ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ በእንግሊዝ ያስፈልጋል ሲሉ ምክራቸውን ሰጥተዋል።

የጤና ሚኒስትሩም የአገሪቷን ሕዝቦች የተቀመጠውን የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲያከብሩ ተማጽነዋል።

ሃንኮክ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ "ሁልጊዜ ገደቡን ባላላን ቁጥር ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

አክለውም "እንደ ማኅበረሰብ በጋራ ልናደርግ የምንችለው በየቤታችን መቆየት ነው" ብለዋል።

በእንግሊዝ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዲወጡ የሚፈቀደው ምግብ ለመግዛት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይንም ከቤታቸው ሆነው መስራት ለማይችሉ ወደ ሥራቸው ለመሄድ ብቻ ነው።

ተመሳሳይ ሕግ በስኮትላንድ፣ በዌልስ እንዲሁም በሰሜን አየር ላንድም ተጥሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ጤና አገልግሎት የሚሰጠው ይህ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት በታሪኩ ትልቁ ነው ተብሏል።

ክትባቱ በቤት ውስጥ እንክብካቤ ለሚያገኙ አዛውንቶች፣ እስከ ጥር ወር አጋማሽ ድረስ ተሰጥቶ ያበቃል የተባለ ሲሆን፤ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ደግሞ እስከ የካቲት ወር አጋማሽ ድረስ የሚሰጥ ይሆናል።