ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ : በዩኬ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ዝግ እንዲሆኑ ተጠየቀ
በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሁሉም የለንደን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ባለቀ ሰዓት ውሳኔ ማስተላለፉ ‹‹ትርምስ ›› ፈጥሯል ተብሏል።
የሐሳብ ለውጡ የመጣው በመዲናዋ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት ጨምሮ በሆስፒታሎች ላይ ጫና መጨመሩን ተከትሎ ነው።
ሚኒስትሮች ትምህርት ቤቶችን መዝጋት "የመጨረሻው አማራጭ" እንደነበረና ትምህርትም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የሌበር ፓርቲ ግን እርምጃው ለተማሪዎች፣ ለመምህራን እና ለወላጆች "ከፍተኛ ጭንቀት" እንደፈጠረ ገልጿል። አንድ ማኅበር ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ጥሪ አቀርቧል።
እንግሊዝ አዲሱን የቫይረሱ ዝርያ ለመቆጣጠር እየተጋች ባለችበት ወቅት በየቀኑ የሚከሰቱ አዳዲስ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አራት ቀናት ከ50 በላይ ሆኗል።
የሮያል የህክምና ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አንድሪው ጎዳርድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አዲሱ ዝርያ በመላው አገሪቱ እየተሰራጨ ሲሆን፤ "በደቡብ ምሥራቅ፣ በለንደን እና ደቡብ ዌልስ ከፍተኛ ጫና ያልነበረባቸው ሆስፒታሎች ዝግጁ መሆን አለባቸው" ብለዋል።
የትምህርት ሚንስትሩ ጋቪን ዊሊያምሰን በታኅሣስ አጋማሽ ላይ በእንግሊዝ ያሉ ሁሉም የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በጥር ወር ወደ ትምህርት እንደሚመለሱ ተናግረው ነበር።
ሆኖም ረቡዕ ዕለት ዊሊያምሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከፍተኛ የኮቪድ-19 ቁጥር የተመዘገበባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አንዳንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትን ጊዜ ይዘገያል ብለዋል።
የገጠማቸውን ጫና ተከትሎ ከሁለት ቀናት በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መዘጋት ወደ መላው ለንደን አስፋፍተዋል።
በዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት ከቤት ይማራሉ ማለት ነው።
ተጋላጭ ተማሪዎች እና ወሳኝ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች ልጆች ትምህርት ቤት መግባታቸውን እንደሚቀጥሉ የገለፀው መንግሥት የቅድመ እንክብካቤ እና ልዩ ድጋፍ ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ አስታውቋል።
መምህራንን የሚወክሉ እና የሠራተኛ ማኅበራት መረጃው የተነገረበትን ጊዜ ተችተዋል።
የሌበር ፓርቲዋ ኬት ግሪን "ትምህረት ከመጀመሩ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ መነገሩ ለወላጆች ትርምስ የሚፈጥር ነው" ብለዋል።
"የጋቪን ዊሊያምሰን ዝቅተኛ ውሳኔ ሰጪነት የታየበት ትምህርት ቤቶችንና ኮሌጆችን የመጀመር ውሳኔ ለወላጆች፣ ለተማሪዎች፣ ለትምህርት ቤቶችና ለኮሌጅ ሠራተኞች ከፍተኛ ጭንቀት እየፈጠረ እና የልጆችን ትምህርት እየጎዳ ነው" ብለዋል።
ብሔራዊ የትምህርት ኅብረት የጋራ ኃላፊ ዶ/ር ሜሪ ቡስተድ ሁሉም የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ጥሪ አቅርበዋል።
"ለለንደን ትክክል የሆነው ነገር ለመላው የአገሪቱ ክፍልም ትክክል ይሆናል" ብለዋል።
በመንግሥት አሃዞች መሠረት ለንደን በዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ ሳምንታዊ የኮሮናቫይረስ ቁጥር የምታስመዘግብ ሲሆን ከ100,000 ሰዎች መካከል 858.5 ቫይረሱ ይገኝባቸዋል። ይህ ቁጥር ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል በእጥፍ ይጨምራል።
የለንደኑ ከንቲባ ሳዲቅ ካሃን ሁሉንም የለንደን ትምህርት ቤቶች መዝጋታቸው "ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ባላለፉት ሁለት ቀናት የተደረጉ ገንቢ ውይይቶችንም" አድንቀዋል።
አንዳንድ የለንደን ትምህርት ቤቶችን ብቻ እንዲዘጉ ለማድረግ የነበረው ዕቅድ "አስቂኝ እና በመዲናዋ ለወላጆች፣ ለመምህራንና ለሠራተኞች ከፍተኛ ግራ መጋባትን የፈጠረ ነበር" ብለዋል።
እግሊዝ ውስጥ አርብ ዕለት 53,285 የሰዎች በኮሮቫይረስ ሲያዙ የ613 ሰዎች ሞትም ሪፖርት ተደርጓል።