ቴክኖሎጂ፡ አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር ከአገልግሎት ውጭ ሆነ

አዶቤ ከእንግዲህ አዲስ አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር የማይለቅ ሲሆን ሰዎችም እንዳይጠቀሙት አሳስቧል

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES/DAVID FIRTH

ታትሟል

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማጫወት ያገለግል የነበረው እና ቀደምት ድረ-ገጾች ይጠቀሙበት የነበረው አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር በይፋ ከአገልግሎት ውጭ ሆነ።

በጎርጎሮሳውያኑ 1996 የተለቀቀው አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር ሰዎች ቪዲዮዎችን ለማሰራጨት እና ጌሞችን እንዲጫወቱ በማገዝ ተወዳጅ ለመሆን በቅቶ ነበር።

ሆኖም ባሉበት የደኅንነት ችግሮች እና ወደ ስማርትፎን ዘመን መሸጋገር አቅቶት ቆይቷል።

አዶቤ ከእንግዲህ አዲስ አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር የማይለቅ ሲሆን ሰዎችም እንዳይጠቀሙት አሳስቧል።

ከጥር 12 ጀምሮ ደግሞ በፍላሽ ፕሌየር የሚሠሩ ቪዲዮዎችን እና አኒሜሽኖችን ማጫወት ያቆማል።

አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር ለምን ተወዳጅ ሆነ?

አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር ወደ ሥራ ሲገባ አብዛኛዎቹ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች የሚያገኙት የግንኙነት ፍጥነት እንዳሁኑ ሳይሆን በጣም ቀርፋፋ ነበሩ፡፡

ፍላሽ ለድረ-ገጽ ዲዛይነሮች እና አኒሜተሮች በአንጻራዊ ሁኔታ በፍጥነት ሊወርድ የሚችል አስደሳች ይዘት ያለው ሥራ እንዲያቀርቡ አግዟል፡፡

"ከ 2 ሜጋ ባይት ባነሰ እና በድረገጽ መፈለጊያ የሚታይ ገጸ-ባህሪዎች፣ ዳራዎች፣ ድምፆች እና ሙዚቃዎች ያካተተ የሦስት ደቂቃ አኒሜሽን መሥራት ይችሉ ነበር" ሲሉ አኒሜተሩ ዴቪድ ፍርዝ አስረድተዋል።

እርሳቸውም ውጤታማ የሆኑ አኒሜሽኖችም ለመሥራትም በቅተዋል፡፡

"የጎደለ መስሎ የተሰማኝን ለማየት የፈለግኩትን ነገሮች አሁን ጨምሬያለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምን ተፈጠረ?

አዶቤ ፍላሽ ፕሌየር ከዚህ ባለፈ እንደ ዩቲዩብ ያሉ ድረገጾች ከፍተኛ ጥራት ያለው ቪዲዮ እንዲለቁ አግዟቸዋል።

በጎርጎሮሳዊያኑ 2009 አዶቤ ፍላሽ ከበይነመረብ ጋር በተገናኙ በ99 በመቶ በሆኑ የዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች ላይ ተጭኗል ብሏል።

ሆኖም በወቅቱ ዓለም ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እየዞረ የበር ቢሆንም አዶቤ ምላሽ ለመስጠት ቀርፋፋ ነበር።

"ፍላሸ ላይትን በመጠቀም ለዝቅተኛ ስልኮች ሠርተን ነበር" ያሉት የቀድሞው የምርቶች ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዴቪድ ሜንዴል ናቸው።

"እንደ ጃፓን ባሉ ቦታዎች በማይታመን ሁኔታ የተሳካ ቢሆንም፣ ከዴስክቶፕ ፍላሽ ጋር ተመሳሳይ አልነበረም፤ ሙሉ ለሙሉ የተዋሃደ አልነበረም።"

በጎርጎሮሳዊያኑ በሚያዝያ 2010 የአፕሉ ስቲቭ ጆብስ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ ፍላሽ በአይፎን እና አይፓድ እንዲሰራ የማይፈቅድበትን ምክንያት አስቀምጧል።

ፍላሽ ለመጠቀም ከባድ፣ አስተማማኝ ያልሆነ፣ የደህንነት ስጋት ያለበት እና በባትሪ ዕድሜ ላይ ተጽዕኖው ከባድ ነበር ብሏል።

በምትኩ ቪዲዮዎችን እና አኒሜሽኖችን በኤችቲኤምኤል 5 እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ማድረስ ይቻል ነበር። ይህም ስማርትፎን ወይም ታብሌት ላይ ፍላሽን ትርፍ ያደርገዋል።

ሜንደልስ "አይፎን ሃሳቡን ሲያቀርብ ፍላሽ ብዙም ዝግጁ አልነበረም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ደግሞም አፕል የአፕል ብቻ የሆነ ሥነ-ምህዳር መፍጠር ፈልጎ ይመስለኛል" ብለዋል።

በመጨረሻም አዶቤ በስማርትፎኖች ላይ የሚሰራ የፍላሽ ማጫወቻውን ይፋ አድርጎ ነበር።

ሆኖም ግን በይነመረቡ ፈጥኖ ሄዶ ነበር። እንደ ፌስቡክ፣ ኔትፍሊክስ እና ዩቲዩብ ያሉ ትልልቅ ተቋማት ቪዲዮዎቻቸውን ያለ ፍላሽ በስማርት ስልኮች መልቀቅ ጀምረው ነበር። በጎርጎሮሳዊያኑ 2011 አዶቤ ለተንቀሳቃሽ ስልኮች ፍላሹን ማዘጋጀት አቆመ።

ለዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ፍላሽ ማምረቱን ቢቀጥልም ሶፍትዌሩ በርካታ የደህንነት ጉድለቶች ተገኙበት።

በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 አፕል ከሳፋሪ ሲያግደው ጉግል ከሮም ደግሞ አንዳንድ የፍላሽ ይዘቶችን ማገድ ጀመረ።

በጎርጎሮሳዊያኑ ሐምሌ 2017 አዶቤ ፍላሽን በ2020 ከአገልግሎት ውጭ እንደሚያደርገው አስታውቆ ነበር።

እንደኤችቲኤምኤል 5 ያሉ ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ለተጠቃሚዎች "ራሱን የቻለ አማራጭ" ለማቅረብ የሚያስችል ብስለት መፍጠር ችሏል።

የድሮ አኒሜሽኖች ምን ይሆናሉ?

አዶቤ ፍላሽ ማጫዎቻዎችን ከጥር 12 ጀምሮ ጥቅም ላይ እንዳይውል ስለሚከለክል፤ ለዓመታት የተሠሩ አኒሜሽኖች፣ ጌሞች እና ድረገጾች ይጠፋሉ የሚል ስጋት አለ።

የጌም ኩባንያው ዚንጋ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ የፋርምቪል ቪዲዮ ጌሙ ፍላሽን ስለሚጠቀም ከ11 ዓመታት በኋላ ዘግቶታል።

ረፍል የተባለ እና በትብብር የሚሠራ ፕሮጀክት ምትክ ሆኖ ማጫወት የሚችል ሶፍትዌር ለማዘጋጀት እየሠራ ነው።

ፍላሽን ከኮምፒውተሬ እንዴት ማስወገድ እችላለሁ?

አዶቤ በዊንዶውስ እና ማክ ኮምፒውተሮች ላይ ፍላሽን ማስወገጃ መመሪያዎችን በድረ-ገጹ አቅርቧል።

"የፍላሽ ማጫወቻ ማስወገዱ ከአገልግሎት ውጭ ከሚሆንበት ቀን በኋላ ለማቅረብ ስለማያስችል ስርዓትዎን ለመጠበቅ ይረዳል" ሲል አስጠንቅቋል።