ዎል ስትሪት ግዙፍ የቻይና ቴሌኮም ኩባንያዎችን አክሲዩን እንዳይሻጥ አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒው ዮርክ አክሲዮን ገበያ ሦስት የቻይና የቴሌኮምዩኒኬሽን ተቋማትን ከቻይና መከላከያ ኃይል ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ሪፖርት በመቅረቡ እንደሚሰርዛቸው አስታወቀ።
ቻይና ሞባይል፣ ቻይና ቴሌኮም እና ቻይና ዩኒኮም ሆንግ ኮንግ በትራምፕ አስተዳደር ጥቁር ነጥብ የተጣለባቸው ተቋማት ናቸው።
እነዚህ ኩባንያዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ከመሰረዛቸው በፊት በኒው ዩርኩ የአክሲዮን ገበያ ያላቸው አክሲዮን ይታገዳል ተብሏል።
ኩባንያዎቹ በአሜሪካ ምንም አይነት እንቅስቃሴ የሌላቸው ሲሆን ሙሉ በሙሉ ገቢያቸውን የሚያገኙት ከቻይና ነው።
እነዚህ ሦስት ኩባንያዎች በአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ላይ ያላቸው ድርሻ እስከዚህም ነው ተብሏል።
ኩባንያዎቹ በቻይና መንግሥት ባለቤትነት ሥር ያሉ ሲሆን በአገሪቱም ትልቅ የገበያ ድርሻ አላቸው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኅዳር ወር የቻይና ወታደራዊ ኃይል ንብረት የሆኑ ወይንም ሠራዊቱ የተወሰነ ድርሻ ባለው ተቋማት ላይ አሜሪካውያን ምንም ዓይነት ሃብት ፈሰስ እንዳያደርጉ አግደው ነበር።
ይህ ትዕዛዝ ፔንታጎን [የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር] ከቻይና ወታደራዊ ተቋማት ጋር ግኙነት አላቸው ሲል ከዘረዘራቸው ኩባንያዎች ጋር አሜሪካውያን ባለሃብቶች ግዢም ሆነ ሽያጭ እንዳያደርጉ ያግዳል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቲክቶክ፣ ሁዋዌ እና ቴንሴንትን ጨምሮ በርካታ የቻይና ኩባንያዎችን ብሔራዊ ደኅንነትን ሰበብ በማድረግ ክልከላ አድርገውባቸዋል።
ቻይና በበኩሏ የአሜሪካ ኩባንያዎችን በመዘርዘር እግድ የጣለች ሲሆን ይህም በሁለቱ ግዙፍ አገራት መካከል የምጣኔ ሃብት ፍጥጫን አጭሯል።
የቻይና ሞባይል፣ ቻይና ቴሌኮም እና ቻይና ዩኒኮም ሆንግ ኮንግ ኩባንያዎች የአክሲዩን ድርሻ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ላይ እንዳይሸጥ ታግዷል።
በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ውስጥ ድርሻቸውን የሚሸጡ የቻይና ኩባንያዎች ቁጥር ከ200 የሚበልጥ ሲሆን አጠቃላይ ዋጋቸውም ከ2.2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ይተመናል።












