ጥቃት፡ በፈረንሳይ አንድ የታጠቀ ግለሰብ ሦስት ፖሊሶችን መግደሉ ተገለፀ

ታትሟል

በፈረንሳይ አንድ የታጠቀ ግለሰብ የቤት ውስጥ ጥቃትን ለማስቆም የተጠሩ ሦስት ፖሊሶችን ተኩሶ መግደሉ ተገለፀ።

የ48 ዓመቱ ተጠርጣሪ ከሕፃናት ማሳደጊያ ጋር በተያያዘ በባለሥልጣናት እንደሚታወቅ የተነገረ ሲሆን፤ በኋላ ላይ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ረቡዕ ማለዳ ላይ አንዲት ሴት ጥቃቱን ሸሽታ ሴንት-ጀስ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሩቅ መንደር ጣሪያ ውስጥ ተደብቃ እንደነበር ተገልጿል።

የታጠቀው ግለሰብ ጥቃቱን ለማስቆም በስፍራው ከደረሱት ፖሊሶች አንዱን ተኩሶ የገደለ ሲሆን፤ በሌላኛው ላይ የመቁሰል አደጋ አድርሷል።

ከዚያም ቤቱ ላይ እሳት በመለኮስ በስፍራው የደረሱ ሌሎች ሁለት ፖሊሶችን ገድሏል። ሴትዮዋን ግን ከአደጋው ተርፋለች።

ጉዳት የደረሰበት ፖሊስ የተመታው እግሩ ላይ ሲሆን፤ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥለው አይደለም ተብሏል።

ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን አገሪቱ የፖሊሶቹን ቤተሰቦች ሃዘን መጋራቷን ተናግረዋል።

የሴንት ጁስት ከንቲባ ፍራንኮስ ቻውታርድ በበኩላቸው ለሊ ፊጋሮ የፈረንሳይ ጋዜጣ፤ ቤቱ መቃጠሉን ገልፀው፤ ባለሥልጣናት ታጣቂው ግለሰብ አምልጦ ይሁን፤ ቤት ውስጥ አብሮ ይቃጠል ለማወቅ እየሞከሩ መሆናቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌራልድ ዳርማኒን በኋላ ላይ ተጠርጣሪው ግለሰብ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን አስታውቀዋል።

የፖሊስ ምንጮች ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቁት ግለሰቡ በመኪናው ውስጥ ሞቶ የተገኘ ሲሆን ራሱን ሳያጠፋ እንዳልቀረ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ ይህ በይፋ አልተረጋገጠም።

ወደ ቦታው ያመሩት ሚኒስትር ዳርማኒንም በመጀመሪያው አደጋ ሕይወቱ ያለፈው የ21 ዓመቱ ብሪግ አርኖ ማቭል እና በሁለተኛው አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ደግሞ የ45 ዓመቱ ሲይረል ሞሬል እና የ37 ዓመቱ ሬሚ ዱፒስ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ በፖሊሶቹ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀው፤ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

ፕሬዚደንት ማክሮንም በትዊተር ገጻቸው "ፖሊሶቹ ሕዝቡን ለመጠበቅ ሲሉ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል፤ ጀግኖቻችን ናቸው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀን ካስቴክስም በትዊተር ገጻቸው "ይህ አሳዛኝ አጋጣሚ መላ አገሪቷን ነክቷል" በማለት የሟች ቤተሰቦችን ሃዘን እንደሚጋሩ ገልፀዋል።

ከሽብር ጋር ባልተያያዙ ጥቃቶች ፖሊሶች ላይ መተኮስ በፈረንሳይ እምብዛም የተለመደ አይደለም።

ከስምንት ዓመታት በፊት በቶሎን አቅራቢያ በምትገኘው ኮሎብሬየሬስ መንደር በስርቆት ከተጠረጠረ ግለሰብ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሁለት ሴት ፖሊሶች መገደላቸው ይታወሳል።