ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሊቢያው ጀነራል ሃፍታር ለወራት ታስረው የነበሩ የጣሊያን ዓሳ አስጋሪዎች ተለቀቁ
የጦርነት ቀጠና በሆነችው ሊቢያ ከሦስት ወራት በላይ ታስረው የቆዩ 18 ዓሳ አስጋሪዎች መለቀቃቸው ተገለፀ።
ይህ የሆነው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስተር ጉሴፔ ኮንቴ በሊቢያ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው።
በሲሲሊ ደሴት የሚኖሩት ግለሰቦቹ ዓሳ በማስገር ላይ ሳሉ ነበር የጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ታማኝ በሆነችው የቅኝት ጀልባ መስከረም ወር ላይ በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
ዓሳ አስጋሪዎቹ ለእስር የተዳረጉት የሊቢያን የውሃ ክልል በሕገ ወጥ መንገድ ጥሳችሏል በሚል ነበር።
ክልሉ ጣሊያን ይገባኛል የምትለው ነው።
ግለሰቦቹ ዓሳ ሲያሰግሩበት የነበረው የሊቢያ ባህር ዳርቻ በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ 'ቀይ ፕራውን' በተባለ የባህር ምግብ የበለፀገ ነው።
ታስረው ከነበሩት 18 ግለሰቦች ስምንቱ ጣሊያናዊ ሲሆኑ፤ ስድስቱ ቱኒሲያዊ፣ ሁለቱ ኢንዶኔዥያዊ እና ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ሴናጋላዊ ናቸው።
የግለሰቦቹ መታሰር ለጠቅላይ ሚኒስትር ጉሴፔ አሳፋሪ ሆኖ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች ለጀነራሉ 'በጣም ተለሳለሱ' በማለት ሲከሷቸው ነበር።
ጀነራል ሃፍታር ዓሳ አስጋሪዎቹን በመልቀቃቸው በምላሹ ያገኙት ነገር ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጉሴፔ ጋር ባንጋዚ የሄዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉጊ ዲ ማኦ በግለሰቦቹ መለቀቅ የተሰማቸውን ደስታ በፌስቡክ ገፃቸው ገልፀዋል።
እርሳቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር ጉሴፔ፤ ጣሊያን ሊቢያ እንድትረጋጋ የሚደረጉ ጥረቶችን እየደገፈች እንደሆነ ለጀነራል ሃፍታር እንደነገሯቸው አክለዋል።
ጣሊያን በጀነራል ካሊፍ ሃፍታርና በትሪፖሊ መንግሥት መካከል ሰላም ለማስፈን በርካታ ሙከራዎችን አድርጋለች።
ግጭቱ በተለይ ከሰዎች ሕገ-ወጥ ዝውውር ጋር በተያያዘ በጣሊያን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።
በርካታ ስደተኞችም ጣሊያን ለመግባት ሲሉ በተጨናነቁና አነስተኛ ጀልባዎች ባህር ለማቋረጥ ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ።
ለረዥም ጊዜ ሊቢያን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ኮለኔል ሙዓመር ጋዳፊ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በኔቶ በሚደገፈው ኃይል ከሥልጣን ከተወገዱና ከተገደሉ በኋላ አገሪቷ የጦርነት ቀጠና ሆናለች።
በአገሪቷን ምስራቃዊ ግዛት የምትገኘውን ባንጋዚ እና ሰፊውን የአገሪቷን ክፍል የሚቆጣጠሩት የጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ኃይሎች በተባበሩት መንግሥታት በሚታወቀውና በትሪፖሊ ከሚገኘው መንግሥት ጋር እየተፋለሙ ነው።