ኢራን አለመረጋጋት እንዲከሰት አድርጓል ያለቸውን ጋዜጠኛ በሞት ቀጣች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን ማህበራዊ የመልዕክት ማስተላለፊያ በመጠቀም ትክከለኛ ያልሆነ መረጃ በማሰራጨት ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለው ያለቸውን ጋዜጠኛ በሞት መቅጣቷ ተሰምቷል።
ሩሆላህ ዛም ዛሬ ቅዳሜ ዕለት ተሰቅሎ ሕይወቱ እንዲያልፍ የተደረገ ሲሆን የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በሰራው ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለው ማለቱን አንድ የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ጋዜጠኛው ነዋሪነቱን በስደት በፈረንሳይ አድርጎ የነበረ ሲሆን እንዴት በቁጥጥር ስር እንደዋለ ግን በግልጽ የተባለ ነገር የለም። ባሳልፈነው ዓመት ወደ ኢራቅ ሲጓዝ በዛው በቁጥጥር እንደዋለም እየተዘገበ ነው።
መንግስትን በመቃወም የሚታወቀው 'አማድኒውስ' ድረ ገጽን በበላይነት ይመራ ነበር ሩሆላህ ዛም።
ኢራን ጋዜጠኛውን በአውሮፓውያኑ 2017-18 ላይ አገር አቀፍ አመጽ እንዲቀጣጠል አነሳስቷል በሚለው ትከሰዋለች።
ሩሆላህ ዛም የሚመራውና ከአንድ ሚሊየን በላይ ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም ትስስር የኢራን ባለስልጣናትን በተመለከተ የተለያዩ መልዕክቶችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ይዘዋወሩበት ነበር።
ምንም እንኳን የኢራን መንግስት የቴሌግራም ትስስሩ እንዲዘጋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሌላ ስም ተመልሶ መጥቷል።
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት የጋዜጠኛውን የሞት ፍርድ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ''ይህ የንግግር ነጻነትን በእጅጉ የሚጋፋና መገናኛ ብዙሀን ላይ ጫና የሚያሳድር ነው'' ሲል ማውገዙን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ጋዜጠኛው በፈረንሳይ ጥገኝነት ተሰጥቶት ሲኖር የነበረ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2009 በኢራን ከተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውሎ በእስር አሳልፎ ነበር። ይህንን ተከትሎም ነው ፈረንሳይ ጥገኝነት የሰጠችው።
አሶሺየትድ ፕረስ ደግሞ ሩሆላህ ዛምበቴሌቪዥን ቀርቦ ለሰራው ስራ ይቅርታ መጠየቁን ዘግቧል።












