ሴቶች ፡ በአርጀንቲና ጽንስ ማቋረጥን የሚፈቅድ ሕግ ከመጨረሻ ምዕራፍ ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በርካታ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ባሉባት አርጀንቲና የሚገኙ ፖለቲከኞች ማቋረጥን የሚፈቅድ አዲስ ሕግ ለማጽደቅ ከጫፍ መድረሳቸው ተሰምቷል።
ጥቂት የማይባሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ለዓመታት ይህ እንዲሆን ሲከራከሩ ነበር።
የአገሪቱ የታችኛው ፓርላማ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈቅደውን ረቂቅ ሕግ 131 ለ 117 በሆነ አብላጫ ድምጽ ተቀብሎታል።
ረቂቁ በይፋ ሕግ ከመሆኑ በፊት ግን በላይኛው ፓርላማ አባላትና ሴኔቱ መጽደቅ ይኖርበታል ተብሏል። ይህ ሊሆን የሚችለውም እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያኑ ዓመት ነው።
አርጀንቲና ውስጥ ጽንስ ያቋረጡ በርካታ ሴቶች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ባቀረቡት በዚህ ረቂቅ መሰረት የአገሬው ሴቶች ጽንሱ 14 ሳምንት እስከሚሞላው ድረስ ማቋረጥ የሚፈቅድ ሲሆን ከ14 ሳምንት በኋላ ግን ጽንሱን ማቋረጥ ይከለክላል።
በአሁኑ ሰአት በአርጀንቲና ጽንስ ማቋረጥ የሚፈቀደው ለተደፈሩ ሴቶችና የጽንሱ መቀጠል የእናትየው ጤናን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይጥለዋል ተብሎ ከታመነ ብቻ ነው።
የታችኛው ፓርላማ ይህንን ረቂቅ ሕግ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እስከ አርብ በቀጠለና 20 ሰአታትን ከፈጀ ክርክርና ውይይት በኋላ ነው በአብላጫ ድምጽ ሊያጸድቀው የቻለው።
''እኔም ካቶሊክ ነኝ፤ ነገር ግን ለሁሉም የሚሆን ሕግ ማውጣት አለብኝ'' ብለዋል ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ። አክለውም ''ይህ በጣም ትልቅ የማህበራዊ ጤና ጉዳይ ነው'' ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት ደግሞ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጽንስ ማቋረጥን እንደሚቃወምና የአርጀንቲና ፖለቲከኞች ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤኑት በማሳሰብ ''ለሕይወት ትርጉም እንስጥ'' ብላለች።
በተቃራኒው የሴቶች፣ ጾታ እና ብዝሀነት ሚኒስትሯ ኤሊዛቤት ጎሜዝ ዘልኮርታ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ''በታሪካችን አዲስ ምዕራፍ ጽፈናል'' ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
እንደ አርጀንቲና መንግስት መረጃ ከሆነ በየዓመቱ 38 ሺ የሚሆኑ ሴቶች በድብቅ ደህንነታቸው ባልተጠበቀ ክሊኒኮች ጽንስ ያቋርጣሉ። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ሕይወት ያልፋል።












