ጠ/ሚንስትር ዐብይ አህመድ ግንባታውን ከጎበኙት የላሙ ወደብ ምን ይጠበቃል?

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የላሙ ወደብ ግንባታን ጎበኙ።
መሪዎቹ በተጨማሪም ዛሬ ሐሙስ በሞምባሳ የተገኝተው ሊኮኒ የእግረኞች መሻገሪያ ድልድይን በይፋ ይመርቃሉ።
1.2 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሞምባሳው ሊኮኒ ድልድይ ለቀጠናው የመጀመሪያው ሲሆን፤ ድልድዩ በ1.9 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወጪ የተገነባ ነው።
ሁለቱ መሪዎች ትላንት በመርሳቤት ግዛት የተገነባውን የድንበር መተላለፊያ መርቀዋል። ከዚያም ወደ ላሙ ግዛት አቅንተው የወደብ ግንባታ ሂደቱን ቃኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት፤ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በድንበር ተሻጋሪ የመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ እንደሚተባበሩ መሪዎቹ ተናግረዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኘውን ባለ 32 ክፍል የላሙ ወደብ በጎበኙበት ወቅት፤ ከሞምባሳ በናይሮቢ አድርጎ አዲስ አበባ የሚገባውን አውራ ጎዳና ለማፋጠን ተስማምተዋል።
ይህ አውራ ጎዳና የቀጠናውን ንግድ ያሳልጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዝደንት ኡሁሩ "የሞምባሳ-ናይሮቢ-አዲስ አበባ አውራ ጎዳና አካል የሆነውን የላሙ ወደብ ግንባታ ቃኝተናል። በዚህ የላፕሴት ፕሮጀክት አማካይነት ኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ቀጥተኛ የሆነ መንገድ ታገኛለች። ሞያሌን፣ ኢሲኦሎን እና የላሙ ወደብን የሚያገናኝ ነው" ብለዋል።
ላፕሴት (LAPSSET) የተባለው ፕሮጀክት የላሙ ወደብን፣ ደቡብ ሱዳንን እና የኢትዮጵያ የትራንስፖርት መተላለፊያን የሚወክል ነው።
ይህ ፕሮጀክት የኬንያ፣ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ነው። ፕሮጅክቱ ሦስቱን አገራት እርስ በእርስ የሚያስተሳስር ሲሆን፤ ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋርም እንደሚያገናኛቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የላሙ ወደብ ለኢትዮጵያ እና ለደቡብ ሱዳን እንደሚጠቅም ተናግረዋል። የሁለቱ አገሮች ትብብር መላው አፍሪካን ለማስተሳሰር የሚደረገው ጥረት አካል እንደሆነም ገልጸዋል።
"የላሙ ወደብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለደቡብ ሱዳንም ይጠቅማል። በቀጠናችን የምጣኔ ሀብት ትስስር ለመፍጠርና የሕዝባችንን ሕይወት ለመለወጥ ያለን ራዕይ እውነት እንዲሆን ያግዛል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗና የአውራ ጎዳና መሠረተ ልማት ውስንነት አገሪቱ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።
"በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ መሠረተ ልማት እና የምጣኔ ሀብት ትስስር መኖር አይቻልም። ምሥራቅ አፍሪካን መቀየር የምንችለው ወንድሜ [ኡሁሩ ኬንያታ] ኬንያ ውስጥ እንዳደረጉት ሁሉ እያንዳንዱ መንግሥት ጊዜና አቅሙን መሠረተ ልማት ላይ ለማፍሰስ ቁርጠኛ ሲሆን ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ በበኩላቸው፤ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ትስስር ለመፍጠር ከተስማሙ በኋላ የላሙ ወደብ ግንባታ በአመርቂ ሁኔታ እየተገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ክፍል እንደተጠናቀቀና የሁለት ተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ 86 በመቶ ማለቁን ተናግረዋል።
"በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ላይ እርስዎን እና የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዝዳንት ጋብዤ የወደቡን ሦስት ክፍሎች እንደምናስጀምር ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ኡሁሩ፤ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተናግረዋል።
ላሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ወደብ ሆኖ የምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የንግድ መዳረሻ እንደሚሆንም ኡሁሩ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ በምን መንገድ በቀጠናው የትራንስፖርት ቢዝነስ እንደሚጣመሩ የሚጠቁም ዝርዝር እቅድ ይፋ እንደሚያደርጉም አክለዋል።
ይህም ምሥራቅ አፍሪካን በቀጠናው እንዲሁም በአፍሪካም የሎጅስቲክስ ዘርፍ ግንባር ቀደም የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ፕሬዘዳንት ኡሁሩ አያይዘውም የላሙ-ዊቱ-ጋሪሰን አውራ ጎዳና 80 በመቶ ተጠናቋል ብለዋል።
ይህ አውራ ጎዳና በጋሪሳ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት አመቺ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህ ቀደም የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን የጎበኙት ፕሬዝዳንቱ፤ ሁለቱ አገሮች ልዩ የምጣኔ ሀብት ማዕከል ሞያሌ ውስጥ ለመገንባት መወሰናቸውን ተናግረዋል። ይህም ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ከማሳደጉ ባሻገር የአካባቢውን ነዋሪዎች እንደሚጠቅም ተገልጿል።
የላሙ ወደብ
ይህ ወደብ የሚገነባው በኬንያዋ ላሙ ግዛት ውስጥ ሲሆን 32 መርከቦች በተመሳሳይ ሰዓት መልህቃቸውን እንዲጥሉ የሚያስችል ነው።
የዚህ ወደብ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት መርከብ ማረፊያዎች ግንባታ ወጪ በኬንያ መንግሥት የሚሸፍን ይሆናል ተብሏል።
የመጀመሪያው መርከብ ማቆሚያ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው እና ሦስተኛዎቹ የመርከብ ማቆሚያዎች ግንባታ ደግሞ በቀጣይ ወራት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይገመታል።
ይህንንም ተከትሎ የላሙ ወደብን ወደ ሥራ ለማስገባ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።












