የራሴን 'አገር' ካልሠራሁ ብሎ ከመንግሥት የተጣለው ግለሰብ ታሪክ ፊልም ሆኖ መጥቷል

የፎቶው ባለመብት, LORENZO ROSA/NETFLIX
ጊዜው በፈረንጆቹ 1960ዎቹ። ቦታው ደግሞ አገረ ጣልያን።
አንድ ወጣት መኃንዲስ በአድሪያቲክ ባሕር ላይ የራሱን ደሴት ይገነባል። 'ምግብ ጀምረናል' የሚል ታፔላ የሰቀሉ ሬስቶራንቶች ይከፍታል፤ መጠጥ ቤት ያስመርቃል፤ አልፎም ፖስታ ቤት ይገነባል።
ይህን ልብ ወለድ የሚመስልን ታሪክ ብዙዎች አያውቁትም።
አሁን ግን ይህ አስደናቂ ታሪክ ኔትፍሊክስ በተሰኘው ፊልም አከፋፋይ ድርጅት ቤትዎ ድረስ ሊመጣ ነው።
'የራስ ወዳዶች ልዑል' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፊልም የጆርጂዮ ሮዛን ታሪክ ይዳስሳል።
ታሪኩ የተፈፀመው በጣሊያኗ ሪሚኒ ከተማ ነው።
ከዚህች ከተማ ባህር ዳርቻ ላይ ነው ጆርጂዮ የራሱን ደሴት አቋቁሞ አገር ካልመሰርትኩ ያለው።
ጆርጂዮ ይህችን ዓለም የተሰናበተው በፈረንጆቹ 2017 ነው። በ92 ዓመቱ።
ነገር ግን ከመሞቱ በፊት የኔትፍሊክስ ሰዎች ወደ መኖሪያ ቤቱ ብቅ ብለው እባክህ ፈቃድህ ከሆነ ያንተን ታሪክ በፊልም ልንሰንደው አስበናል አሉት።
ጆርጂዮ ይህ ጥያቄ ሲቀርብለት ትንሽ አንገራገረ። ከጥቂት ልመና በኋላ ግን ፈቃደኝቱን አሰማ።
ፊልሙ ጆርጂዮ እንዴት ደሴት እንደቀለሰ፤ ይደምሰስ የሚለውን የመንግሥት ውሳኔ እንደቀለበሰ የሚያሳይ ነው።
ጆርጂዮ የራሴን ብዙ እሳት የማትፈጅ አገር ካልመሰርትኩ ያለው በ9167 ነው።
ደሴቷ የነፃነት አርማ እንድትሆንም አቅዶ ነበር ሰውዬው።
በወቅቱ ብዙዎች ገላመጡት፤ አብደህ መሆን አለበት የሚልም አስተያየት ሰጡት።
ነገር ግን የጆርጂዮ ልጅ አባቴ 'አይሶላ ዴሌ ሮዛን' ለመቀለስ የተነሳው እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ አይደለም ይላል።
"አባቴን ብታውቁት ኖሮ. . . በጣም ጥንቁቅ እና የተደራጀ መኃንዲስ ነበር። እርግጥ ነው ትንሽ ወጣ ያለ ባህሪ ነበረው። ነገር ግን የራሱን መድረክ መገንባት ይፈልግ ነበር። ይህ ነው የራስ ወዳዶች ልዑል ያስባለው" ይላል ሎሬንዞ ሮዛ።

የፎቶው ባለመብት, SIMONE FLORENA
ደሴቷ በ400 ስኩዌር ሜትር ላይ የተገነባች ናት። ከባህር ጠለል 26 ኪሎ ሜትር ከፍ ብላ ነው የተገነባችው።
ከሪሚኒ ጠረፍ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ገባ ብላ ትገኛለች። ይህ ማለት ከጣልያን ግዛት ውጭ ናት ማለት ነው።
ጆርጂዮ ሮዛ ራሱን የደሴቲቱ ፕሬዝደንት አድርጎ ሾመ። የሮዝ ደሴት ሪፐብሊክ ሲልም 'ነፃ አገር' አወጀ።
ይህ ግን ለጣልያን መንግሥት አልተዋጠም። እንዴት ፈቃድ ሳይጠይቅ አገር ይገነባል? በዚያ ላይ ከቱሪዝም ቤሳ ይሰበስባል ሲሉ ተቆጡ።
አንዳንድ ባለሥልጣናት ደሴቲቱ የቁማርና የስካር መንደር ሆናለች። ምን እሱ ብቻ ለሶቪዬት ሕብረት የባህር ጠላቂ ዋናተኞች መደበቂያ ሆናለች ሲሉ ከሰሱ።
ጆርጂዮ ነፃ ደሴት ባወጀ በ55ኛ ቀኑ የጣልያን መንግሥት ወደ ደሴቷ ወታደር ላከ። ጆርጂዮ ላቡን ጠብ ያደረገባትን ደሴት በዳይናማይት ድብልቅልቋን አወጡት።
ጆርጂዮ ደሴቷን ሲገነባ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር።
የጣልያን ጋዜጦች ከቪዬትናም ጦርነት ይልቅ የደሴቷን ብርቅርቅነት የፊት ገፃቸው ማጀቢያ አደረጓት።
ወጣቶች ከአራቱም የዓለም አቅጣጫዎች ወደ አዲሷ የነፃነት ደሴት ይጎርፉ ጀመር።
ጆርጂዮ ከቱሪዝም የሚያገኘውን ገቢ ልቁረጥ የሚል መንግሥት አልነበረውም። መንግሥት እሱ ራሱ ነበር።
ብዙዎች ይህ ድርጊቱ ነው የጣልያን ባለሥልጣናትን ያስቆጣው ብለው ይገምታሉ።
ሰውዬው ከጣልያን መንግሥት ጋር የገባው እሰጥ-አገባ ጭራሽ ትኩረት ሳበለት።
መኃንዲሱ ጆርጂዮ ደሴቷን ለመግንባት ብዙ ላብና ገንዘብ አፍስሷል። የዴሴቷ ዲዛይን ልዩ ነው እየተባለም ይሞካሽ ነበር።
ነገር ግን ጆርጂዮ ስንት የለፋባት ምድር ስትወድም ከተመለከተ በኋላ ቅስሙ ተሰበረ። ስለ ደሴቲቱ ማውራትም ሆነ ማሰብ አይሻም ነበር ይላል ልጁ ሎሬንዞ።
በጣልያን መከላከያ ሠራዊቷ የወደመችው ደሴት አፅም ግን አሁንም ከባህር በላይ ተንሳፎ ይታያል።












