ጆ ባይደን የፕሬስ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ በሴቶች ቡድን እንዲመራ ወሰኑ

ጆ ባይደን የፕሬስ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ በሴቶች ቡድን እንዲመራ ወሰኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፕሬስ ጉዳዮች ቢሮን ሙሉ በሙሉ በሴቶች እንዲመራ አደረጉ። ይህ በአሜሪካ ታሪክ አዲስ ነገር ነው ተብሏል።

ይህንን ቡድን የሚመሩት ኬት ቤዲንግፊልድ ናቸው። ሚስስ ኬቲ የምረጡኝ ቅስቀሳው የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ነበሩ።

የባራክ ኦባማ የዋይት ሐውስ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የነበረችው ጄን ሳኪ ደግሞ ፕሬስ ሴክሬተሪ ሆና ተሰይማለች።

ባይደን በአስተዳደራቸው ሴቶች ተገቢውን ቦታ እንዲያገኙ እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ነበር።

ባይደን ለሚዲያ በላኩት መግለጫ " ዋይት ሐውስ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ቡድን እንዲመራ መወሰኔን ስገልጽ ታላቅ ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል።

ጨምረውም፤ እነዚህ የበቁና የነቁ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ልምድና ችሎታቸውን ተጠቅመው ይህን አገር ወደነበረበት አቋም ይመልሱታል ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

የካመላ ሐሪስ የፕሬስ ጉዳዮች ረዳት የነበሩት ሳይሞን ሳንደርስና አሽሊ ኤቲየን በዚህ ቡድን ውስጥ ተካተዋል።

ባይደን የነዚህን ሴት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ሥልጣን በሴኔቱ ማጸደቅ አይጠበቅባቸውም። ሴኔት የሚያጸድቀው የካቢኔ ሚኒስትር እጩዎቻቸውን ብቻ ነው።

ጆ ባይደን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ቁልፍ የአገሪቱን ሥልጣን የሚቆጣጠሩ ስሞችን ከወዲሁ ይፋ አድርገዋል።

እያዋቀርኩት ያለው ካቢኔ አገራችን አሜሪካን ወደነበረችበት ክብር የሚመልስ ነው ሲሉ ባይደን ተናግረዋል። ይህም ዶናልድ ትራምፕ አገሪቷን ወደ ኋላ እንደጎተቷት ለማስገንዘብ የሰነዘሩት አስተያየት ነበር።

ጆ ባይደን ትናንት እሑድ ሜጀር ከሚጠሩት ውሻቸው ጋር ሲጫወቱ ተንሸራተው በመውደቃቸው መጠነኛ የእግር አጥንት መሰንጠቅ እንዳጋጠማቸው።

ጆ ባይደን 78 ዓመታቸው ነው።

ጉዳቱ የከፋ እንዳልሆነና ነገር ግን የመራመጃ ጫማ ለቀጣይ ሳምንታት እየተጫሙ ክትትል እንደሚደረግላቸው ተነግሯል።

በጃንዋሪ 20 ባይደን የአሜሪካ 46ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል።

ዛሬ ሰኞ ባይደን ለመጀመርያ ጊዜ የአገሪቱን ከፍተኛ የደኅንነት ምስጢሮችና ቁልፍ መረጃዎችን ከደኅንነት ኃላፊዎች ማብራሪያ ይሰጣቸዋል።

ይህም የሆነው ትራምፕ የሽግግር ሥራው እንዲጀመር ለሚመለከተው መሥሪያ ቤት በጀት መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።