ፊፋ ፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በፊፋ ለአምስት ዓመት ታገዱ

ታትሟል

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት አህመድ የተለያዩ የሥነ ምግባር ደንቦችን በመጣስ ፊፋ የአምስት ዓመት ዕገዳ ጣለባቸው።

የፊፋ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት የ60 ዓመቱ አህመድ የፊፋን የታማኝነት ግዴታን፣ ስጦታ መቀበልና መስጠትን፣ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀምና የተቋሙን ንብረት አላግባብ መጠቀምን የመሳሰሉትን ደንቦች በመጣሳቸው ነው የታገዱት።

ፊፋ ያወጣው መግለጫ አንዳለው "በአህመድ ላይ በሦስት ዓመታት ዓመታት ውስጥ ወደ መካ ለተደረጉ ሐይማኖታዊ ጉዞዎች የወጣ ወጪንና የስፖርት ቁሳቁሶች አምራች ድርጅት ከሆነው ታክቲካል ስቲል ከተባለው ተቋም ጋር የተደረሰውን ስምምነት ጨምሮ ከካፍ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች ላይ ምርመራ ተደርጓል።"

በአህመድ ላይ ከዕገዳ በተጨማሪ የ200 ሺህ ዶላር ቅጣትም ተጥሎባቸዋል። ነገር ግን እሳቸው ምንም አላጠፋሁም ሲሉ ይከራከራሉ።

የማዳጋስካር ዜጋ የሆኑት አህመድ የዕገዳ ውሳኔው ከደረሳቸው በኋላ ለዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) አቤት ማለት የሚችሉ ሲሆን ሂደቱም እስከ ሁለት ወራት ሊወስድ ይችላል ተብሏል።

የቀድሞው የማዳጋስካር የእግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝዳንት የነበሩት አህመድ ባለፈው ወር በሚመጣው መጋቢት በሚካሄደው የካፍ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድድር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለመወዳደር ፍላጎት እንዳለቸው አሳውቀው ነበር።

ለድጋሚ ምርጫ የመወዳደር ዕድላቸው ግን የሚወሰነው ለፍርድ ቤት በሚያቀርቡት አቤቱታ በመርታት ብቻ ሳይሆን፤ የጉዳያቸው የዕጩዎች መቀበያ ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ዕልባት ካገኘ ብቻ ነው።

አህመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከዳኑ በኋላ የጤና ሁኔታቸውን በመግለጽ ለማገገሚያ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚፈልጉ አሳውቀው የካፍ ኃላፊነታቸውን ለምክትላቸው አስተላልፈዋል።

የካፍ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ኮንስታንት ኦማሪም ኃላፊነቱን በመያዝ የአህጉሪቱን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን እየመሩ ይገኛሉ።