አሜሪካ አበረታች መድኃኒት የሚጠቀሙ ስፖርተኞችን በወንጀል ልትከስ ነው

ግሪጎሪ ሮድቼንኮቭ
የምስሉ መግለጫ, ግሪጎሪ ሮድቼንኮቭ
ታትሟል

የአሜሪካ ምክር ቤት ሴኔት በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ የአበረታች መድኃኒት የተጠቀመ ማንኛውንም ሰው የወንጀል ክስ እንዲመሰረትበት የሚያስችልን ረቂቅ ህግ አፀደቀ።

የአበረታች መድኃኒት ጥሰቶችን ባጋለጠው በሩሲያዊው ግሪጎሪ ሮድቼንኮቭ ስም የሮድቼንኮቭ ፀረ-አበረታች አዋጅ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲፈርሙበት ሕግ ይሆናል ተብሏል፡፡

የአሜሪካ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ዋና ኃላፊ ትራቪስ ታይጋርት ውሳኔውን “ንፁህ ስፖርት ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ትልቅ” ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የዓለም ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) ግን ጉዳዩ እንዳሳሰበው አስታውቋል።

ቀደም ሲል በተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ከፀደቀ በኋላ ሰኞ ዕለት ሴኔቱ ያለተቃውሞ ያፀደቀው ሕግ ስፖርተኞችን፣ ስፖንሰር አድራጊዎችን እና ከአበረታች መድኃኒት መስፋፋት ጀርባ ያሉት ላይ አሜሪካ ክስ መመስረት ያስችላታል።

ሕጉ ቀድም ሲል በዋዳ ቅጣት ካልተላፈባቸውን ስፖርተኞች ይልቅ አሰልጣኞች፣ ወኪሎች፣ ሥራ አስኪያጆች እና ባለሥልጣናትን ላይ ዒላማ ያደርጋል፡፡

ህጉን ተከላለፉ አካላት እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ወይም እስከ 10 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣትን ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

“ሕጉ ንፁህ ስፖርተኞችን ለመከላከል እንዲሁም ስፖርትን፣ ስፖንሰሮችን የሚያታልሉ እና ስፖርተረኞችን የሚጎዱ ዓለም አቀፍ የአበረታች መድኃኒት አሰራጮችን ተጠያቂ ያደርጋል” ብለዋል ታይጋርት፡፡

“በዓለም ዙሪያ ለንጹህ ስፖርት ለሚደረገው ትግል ታላቅ ቀን ነው። በቅርቡ ህግ ሆኖ ለማየት እና ለንጹህ ስፖርት በመፍጠር በኩል ለውት ያመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ዋዳ በበኩሉ ዓለም አቀፋዊ የፀረ-አበረታች መድኃኒት እርምጃዎችን ሊያዳክም ይችላል በሚል “ሥጋቶች” እንዳሉት ገልጿል።

ሕጉ በረቂቁ ውስጥ ያካተታቸውን የአሜሪካ ፕሮፌሽናል እና የኮሌጅ ስፖርተኞችን ሳያካትት ለምን ቀረ ሲል ጠይቋል፡፡

“ለአሜሪካውያን ስፖርቶች ጥሩ ካልሆነ ለሌላው ዓለም ጥሩ የሆነው ለምንድነው?” ሲልም ያክላል።

በተጨማሪ ይህ ረቂቅ ሕጉ መረጃ ሰጪዎች ወደ ፊት እንዳይመጡ ሊያግደው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ዋዳ ገልጿል።

ታይጋር ግን ህጉ “መረጃ ሰጪዎችን ይጠብቃል” ብሏል፡፡

የቀድሞው የሞስኮ የፀረ-አበረታች መድኃኒቶች ቤተ ሙከራ ኃላፊ የነበረው ሮድቼንኮቭ እ.ኤ.አ. በ2015 በሩሲያ መንግስት የተደገፈውን አበረታች መድኃኒት አጠቃቀም ዝርዝር ማስረጃ ይዘው ከሩስያ ተሰደዋል፡፡

በዚህ ምክንያትም ሩሲያ ከ2018ቱ ክረምት ኦሎምፒክ ታግዳለች።