ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጄሪ ራውሊንግስ አረፉ
የጋና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጄሪ ጆን ራውሊንግስ በ73 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
ጄሪ ጆን ራውሊንግስ ሁለት መፈንቅለ-መንግስቶችን መርተዋል፤ የመጀመሪያውም በጎሮጎሳውያኑ 1979 ነው።
በመቀጠል ግን በርካታ ፓርቲዎች በተሳተፉበት ሁለት ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል።
በርካቶች ግርማ ሞገስ የተላበሱ የሚሏቸው መሪው በመጀመሪያ ፕሬዚዳንትነታቸው ወቅትም ሙስናን እታገላለሁ በሚል ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረጋቸው ሊመረጡ ችለዋል።
በስልጣንም ላይ እያሉ በርካታ የቀድሞ አመራሮችን ከሙስናና ገንዘብ ብክነት ጋር በተያያዘ በሞት ቀጥተዋቸዋል።
በህዝቡ ዘንድ የድሃው አለኝታና ደጋፊ ተደርገው ቢታዩም በአገዛዛቸው ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደርሰዋል ብለውም የሚተቿቸው አሉ።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት በመዲናዋ አክራ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ለአጭር ጊዜ ሲታከሙ ቆይተው ህይወታቸው እንዳለፈ ሪፖርትም እየወጣ ነው።
በጋና የአየር ኃይል ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩት ጄሪ ጆን ራውሊንግስ በጎሮጎሳውያኑ 1979 መፈንቅለ መንግሥት መርተው ወታደራዊ ስርአትን ከገረሰሱ በኋላ ለሲቪል መሪ ስልጣኑን አሸጋግረዋል።
ከሁለት አመት በኋላ ሌላ መፈንቅለ መንግሥት በመምራት የወታደራዊ ቡድን ኃላፊ የሆኑ ሲሆን በ1992 በርካታ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ምርጫ እንዲካሄድ አስችለዋል።
በዚህም ወቅት ፕሬዚዳንት ሆነው ለመመረጥ ችለዋል። ለሁለት ጊዜ ያህል በስልጣን ከቆዩ በኋላ ከመሪነታቸው በጎሮጎሳውያኑ 2001 ወርደዋል።
ወደ ስልጣን ሲመጡ ጥብቅ በሚባል የሶሻሊስት ርዕዮተ አለም አገሪቷን ይመሩ የነበረ ቢሆንም ወደ በኋላ ግን ነፃ የገበያ ማሻሻያዎችን አድርገዋል።
በጋና እስካሁን የቀጠለውና የሰፈነውን የፖለቲካ መረጋጋት አምጥተዋል የሚባሉት የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ በተለይም በጎሮጎሳውያኑ 1960ዎቹና 70ዎቹ በተከታታይ መፈንቅለ መንግሥት ስትናጥ ለነበረችው ጋና መፍትሄ አምጥተዋል ተብለውም ይመሰገናሉ።