የቀድሞ የታንዛኒያ የፓርላማ አባል ወደ ኬንያ ከሸሹ በኋላ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ታትሟል

የቀደሞው የታንዛኒያ የፓርላማ አባል ጋድብለስ ለማ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ከተሻገሩ በኋላ እሁድ ምሽት በኬንያ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ማሳለፋቸውን የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

የፓርላማ አባሉ የኬንያ ፖሊስ ከታንዛኒያ አቻቸው በደረሰው ጥቆማ ከድንበር 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ ሊያዙ እንደቻሉ ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል።

የፓርላማ አባሉ ጋድብለስ፤ የተያዙት ጠበቃቸው ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ እየወሰዷቸው ሳለ ነበር። ባለቤታቸውና ልጆቻቸውም አብረዋቸው ነበሩ።

ጋድብለስ ለታንዛኒያ የኢምግሬሽን ባለሥልጣናት ፓስፖርታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልነበሩም ተዘግቧል።

ጋዜጣው ጠበቃቸው ጆርጅ ሉችሪ ዋጃኮያህ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ፖለቲከኛውን ናይሮቢ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢሮ ለማቅረብ መፈለጋቸውን ተናግረዋል።

የፓርላማ አባሉ "አሁን ላይ ከባለቤቴ ኔማ፣ ከ14 ዓመቱ ወንድ ልጄ አልብለስ፣ ከሴቷ ልጄ ብሪሊያንስ እና ከመጨረሻው ልጄ ቴሬንስ ጋር ነኝ። ነገ ምን እንደሚሆን አላውቅም። አሁን ላይ ጥገኝነት የሚሰጠኝ እሻለሁ" ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

በታንዛኒያ በተካሄደው ምርጫ ፕሬዚደንት ጆን ማጉፉሊ በከፍተኛ ድምፅ እንደገና መመረጣቸውን ተከትሎ በታቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና አለ።

የቀድሞ የፓርላማ አባሉ ገድብለስም ባለፈው ሳምንት ከእስር ከተለቀቁ ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ ሲሆኑ፤ ፖለቲከኞቹ ታስረው የነበሩት አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የሚጠይቅ ሰልፍ መጥራታቸውን ተከትሎ ነው።