ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያውያን የትራምፕን አስተያየት በመቃውም በለንደን ሰልፍ ወጡ
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን አስተያየት በመቃውም ኢትዮጵያውያን በለንደን የተቃውሞ ሰልፍ ወጡ።
በዩናትድ ኪንግደም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የትራምፕን አስተያየት በመቃውም ለንደን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ነው ሰልፍ ያካሄዱት።
ባሳለፍነው ሳምንት፤ ሱዳን እና እስራኤል የሰላም ስምምነት መድረሳቸውን በማስመልከት ትራምፕ በዋይት ሃውስ የሁለቱን አገራት መሪዎች ጋዜጠኞች በተገኙበት በስልክ ሲያነጋግሩ፤ "ግብፅ የሕዳሴ ግድቡን ልታፈነዳቸው ትችላለች" ማለታቸው ይታወሳል።
በዚህ የፕሬዝደንቱ አስተያየት የተበሳጩ ኢትዮጵያውያን ትናንት "የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኔ ነው!"፣ "አሜሪካ ገለልተኛ አይደለችም" የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ሰልፍ ወጥተዋል።
ሰልፈኞቹ ፕሬዝደንት ትራምፕ ለግዴለሽ ንግግራቸው ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
"በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ የሰጡትን አስተያየት እንዲያስተባብሉ እና ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ ለማቋረጥ የወሰኑትን ዳግም እንዲያጤኑት እንጠይቃለን" ይላል በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያውን ማህበር ያወጣው መግለጫ።
የዶናልድ ትራምፕን አስተያየት ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ "ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ወዳልሆነ ስምምነት ውስጥ እንድትገባ የሚሰጡ ጠብ አጫሪ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም" ያለ ሲሆን፤ ጨምሮም "ኢትዮጵያ ለማንኛውም ማስፈራሪያ አትንበረከከም እንዲሁም በቅኝ ግዛት ለተመሰረተ ውልም እውቅና አትሰጥም" በማለት አስፍሯል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረውን የ130 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መሰረዙ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በአሜሪካ እና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየውን የሕዳሴ ግድብ ድርድር ጥላ መውጣቷ ይታወሳል።
በአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር የሚመራው ድርድር ከሰባት ወራት መቋረጥ በኋላ በዚህ ሳምንት ቀጥሎ መካሄዱም አይዘነጋም።