በኮቪድ-19 ማዕከላት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች የተገባልን ቃል አልተፈጸመም አሉ

ታትሟል

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሥር በሚተዳደሩ እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በተቋቋሙ የሕክምና መስጫዎች ውስጥ የሰሩ እና የሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ የተገባላቸው ቃል እንዳልተፈጸመ በመግለጽ ቅሬታቸውን አቀረቡ።

ኮሮናቫይረስ ወረርሽን በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ መንግሥት በሕክምና ባለሙያዎችን ላይ የሚኖረውን ጫና ከግምት በማስገባት ከባለሙያዎቹ ጎን እንደሚቆም አስታውቆ ነበር።

በዚህ መሠረትም የሚንስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 14/2012 ዓ. ም ባካሄደው 83ኛ መደበኛ ስብሰባ የኮቪድ-19 ወረርሽንን በመከላከል እና የህክምና አገልግሎት በመስጠት በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ባለሙያዎች ልዩ አበል እንዲከፈላቸው ውሳኔ ማሳለፉን ባለሙያዎቹ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ እንደሙያቸው እና ሥራቸው ሁኔታ ከ1ሺህ150 ብር ጀምሮ እስከ 300 ብር በየቀኑ እንዲከፈላቸው ነው የወሰነው።

በዚህ መሠረትም በፌደራል ደረጃ የሚተዳደሩት እንደ ኤካ ኮተቤ፣ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ሚሊኒየም ሆስፒታል ያሉት የጤና ተቋማት እና አንዳንድ ክልሎች ወሳኔውን መሠረት በማድረግ ለባለሙያዎቻቸው ልዩ አበል እንደከፈሉ ባለሙያዎቹ አስታውቀዋል።

ሆኖም በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሥር ከሚተዳደሩ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች መከካከል የተወሰኑት የኮሮናቫይረስ ህክምና መስጫ ማዕከል ሆነው እያገለገሉ ቢሆንም ለባለሙያዎች እስካሁን ምንም ዓይነት ከፍያ እንዳልተፈጸመ የጤና ባለሙያዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ግንቦት አጋማሽ መመሪያው ከወጣ በኋላ የባለሙያ እና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የአበል ዝርዝር በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ደረጃ አልወጣ ሲል ጠብቀን መታገል ጀመርን" ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የጉቶ ሜዳ ኮቪድ -19 ማዕከል ሠራተኛ የሆኑት አቶ ዲኖ ጀማል ናቸው።

ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ከእያንዳንዱ የኮቪድ -19 ህክምና ማዕከል 3 ተወካይ በመምረጥ አቤቱታቸውን ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አስገብተዋል።

ወኪሎቻቸውን ያላሳወቁትን ሳይጨምር 1158 ሠራተኞች ወኪሎቻቸውን መርጠው ልዩ አበሉ ለምን እንዳልተከፈላቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

ኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ገባ ተብሎ ሰዉ በሚሸሽበት ወቅት ጭምር ሙያዊ ግዴታ በሚል ወደ ሥራ መግባታቸውን የገለጹት የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ባልደረባ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሰሩ ጤና ባለሙያዎች ተወካይ የሆኑት አቶ ከድር ሳሊህ ናቸው።

"ሁሉም እኛን ማሞካሸት ጀመረ። በመሃል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኮቪድ -19 ላይ ለሚሰሩ ልዩ አበል ይከፈል አለ። እኛ ሙያዊ እና ሰብዓዊነት ነው ያስገባን። ክፍያ አይተን አይደለም። አንዳንድ ቦታ ይከፈላል ሌላ ቦታ አይከፈልም" ብለዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ጠቅላላ ሐኪም በበኩላቸው በኮሮናቫይረስ ማዕከል ከአምስት ወር በላይ እንደሠሩ እና አሁን ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

መጀመሪያ ላይ ህብረተሰቡ በነበረው ፍራቻ እና በተለያየ ምክንያት ብዙዎች ከቤት እና ለተወሰነ ቀን ብቻ ከሥራ ቦታቸው እንዲሠሩ በተደረገበት እና ትርፍ ክፍያ ባልነበረበት ወቅት ጭምር መሥራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም ሥራ ጀምረው ከሁለት ወራት በኋላ ተግባራዊ እንዲሆን የወጣው መመሪያ ተባግባራዊ አለመሆኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል።

"ማህበረሰቡ ባለሙያው ብዙ ክፍያ እንዳለው ነው የሚያውቀው። የማይከፍሉ ከሆነ ማህበረሰቡ ማወቅ አለበት። ቢከፍሉን ጥሩ ነው። የማይለከፍሉ ከሆነ ግን አንከፍልም ግን እናመሰግናለን የሚል ደብዳቤ ቢሰጠን። ከህክምና ጣቢያው ስወጣ በግሌ የሚያስጠሉ ፈተናዎች ነበሩት። 'የት ነበርሽ?' ምናምን የሚሉት ነገሮች ትንሽ ቅስም ይሰብራል" ብለዋል ሐኪሟ።

እንደ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ ልዩ አበሉ ባይከፈልም በፌደራል ስር በሚገኙ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከላት እና በአንዳንድ ክልሎች ተግባራዊ መደረጉን ግን እነዚህ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

"አዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሄደው ያነጋገሩ ባልደረቦች አሉ። እነሱ ግን በቃ እንደማይገባን ነገሩን ያሉት። በጀት የለንም አሉ። በጀት ከሌለ መጀመሪያም ውሳኔው (የሚንስተሮች ምክር ቤት) አይፈቅድም" ብለዋል።

ውሳኔውን መሠረት በማድረግ ጤና ቢሮው ክፍያውን እንዲፈጽምላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ተገቢውን ምላሽ አላገኙም።

ክፍያው ሁለት ቢሊዮን ብር ገደማ ስለሚሆን እንደሚክብዳቸው፤ ከኮቪድ-19 ማዕከላት ውጭ ያሉት ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን ጭምር በመግለጽ እነሱን ስለማያካትት ለአፈጻጸም አመቺ አይደለም ተብሎ ከጤና ቢሮው እንደተመለሰላቸው አቶ ዲኖ አስታውቀዋል።

የጤና ጥበቃ ሚንስትር ደግሞ ጉዳዩ እንደማይመለከተው እንዳስታወቃቸው እና ለከተማው ካቢኔ ደብዳቤ አስገብተው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሚንስትሮች ምክር ቤት በመመሪያው ያወጣው በኮሮናቫይረስ የተያዙን የሚያክሙ፣ በለይቶ ማቆያ ህክምና በመስጠት ላይ የሚገኙ፣ ቀጥታ ተጋላጭ ሆኑ ባለሙያዎች በሚል በዝርዝር ለይቶ ማስቀመጡን ገልጸዋል።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ግን አሠራሩን በመቀየር ቢሮ የሚሠሩትን ተጠቃሚ በማድረግ ሌላ ውሳኔ ተግባራዊ መደረጉን ኮንነዋል።

'የወጣው ውሳኔ ሁሉንም ባያካትትም ሁሉም የህክምና ባለሙያ ለኮቪድ-19 ተጋላጭ ነው' በሚል ቢሮ ውስጥ ያሉትንም ለመጥቀም የሚመስል ሁሉንም የሚያካትት አሠራር ለመፍጠር መሞከሩን አቶ ከድር አስታውቀዋል።

ስለ ጉዳዩ ለሲቪል ሰርቪስ ያቀረቡት ቅሬታ ደግሞ 'ካልተስማማችሁ መልቀቅ ትችላላችሁ ብዙ ሥራ የሚፈልግ ባለሙያ አለ' በሚል ምላሽ አንደተሰጣቸውም ገልጿል።

የቤት ጉዳይ

የጤና ባለሙያዎቹ ሌላ ቅሬታ ደግሞ የቤት ጉዳይ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተገንብተው የተጠናቀቁና በግንባታ ላይ ያሉ በርካታ ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሶ፤ በራሳቸውም ሆነ በባለቤቶቻቸው ስም ቤት እንደሌላቸው የሚገልጽ ማስረጃ እንዲያቀርቡ መጠየቁን አስታውሰዋል።

መረጃውን ለሟሟላትም ውጣ ውረድ በማሳለፍ በተሰጣቸው ጥቂት ቀናት መረጃውን ማስገባታቸውን ገልጸዋል።

ዕጣ እንደሚወጣላቸው በተነገራቸው ሰሞን የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ችግር ምክንያት መደናቀፉን አስታውቀዋል። ምላሽ እንገኛለን በሚል ቢጠብቁም የቀድሞው ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከቦታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ ተቀይረዋል።

በኋላ የተሰጣቸው ምላሽ 'ዳታ' ለመስብሰብ ነው የሚል ነበር።

ቤት እናገኛለን በሚል መረጃ ለማቅረብ ተሯሩጠው 'ለዳታ ነው' መባላቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ጠቅሰዋል። መጀመሪያ ተስፋ ስለተሰጣቸው እንጂ ያሰቡት ባይሆንም ቃል ከተገባ ደግሞ ሊፈጸም ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።

ሰኔ 2012 ዓ. ም የጤና ባለሙያው በሦስት ቀን ውስጥ በራሳቸው እና በትዳር አጋራቸው ስም ቤት እንደሌላቸው የሚገልጽ ማስረጃ አምጡ መባላቸውን አቶ ዲኖ ገልጸው "አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ለህክምና ባለሙያዎች ቤት ሊሰጥ ነው ሁሉ ብለዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

"አንዳንድ ታካሚዎች ቤት ተሰጣችሁ ደስ ብሎናል እስከሚሉ ድረስ። እኛ ላይ የማታለል ሠራ ነው የሰረቡን" ብለዋል።

በራሳቸውም ሆነ በትዳር አጋሮቻቸው ስም ቤት እንደሌላቸው የሚያሳይ ማስረጃ አስገብተው ዕጣው ሊወጣ አካባቢ በአርቲስት ሃጫሉ ሞት ምክንያት ዘገየ ሲሉ ያስታወሱት አቶ ከድር ናቸው።

ከህክምና ቦታቸው ወጥተው ሰዎች ከኮቪድ-19 ማዕከላት በመምጣታቸው ብቻ እያገለሏቸው እና በአጭር ቀናት ውስጥ ያስገቡትን ማስረጃ "ለዳታ ነው። ምን ያህል ቤት እንደሌላችሁ ለማወቅ ነው እንጂ ቤት ይሰጣችኋል አልተባለም" መባሉ እንዳሳዘናቸውም አስታውቀዋል።

የህክምና ዶክተሯ በበኩላቸው "ቤት እንሰጣለን ብለው ወከባ ፈጠሩ። እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ጤና ባለሙያ ግን ከቤት ውጣ የተባለ ሃኪም አለ። በኮቪድ-19 ጊዜ ቤት ልንሰጥ ነው ብለው የኑሮ ውድነት እንዲመጣ፤ ጤና ባለሙያዎች የሚከራየውን ቤት በእጥፍ እንዲጨመረበት ነው ያደረጉት። ይከፈላቸዋል በሚል ብቻ የኑሮ ውድነት እንዲጨምርበት ተደርጓል" ብለዋል።

የገቢ ግብር ቅነሳ

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ጠቅላላ ሐኪም የገቢ ግብር እስካሁን እንዳልተነሳ እና በየትኛውም ህክምና ተቋም የሚከፈለው 'ዲዩቲ' (የሥራ) አበል አንኳን በአግባቡ እንዳልተከፈላቸው አስታውቀዋል።

"ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው ከተባለም ይህ መሸፈን ያለበት በጤና መድህን ነው። ቤተሰቦቻችን እየተከፈላችሁ ነው። ቤተሰብ እና ጓደኞቻችን የት አደረጋችሁት እያሉ ነው። እነሱ ባወጡት ህግ ነው የጠየቀውነው። ለምን ይሸራርፉታል በሚል። ህዝቡ በአዋጁ እየተጠቀማችሁ ነው እያለ ነው። ቤተሰብም ጓደኛም ግብርም ቀርቶላችኋል ይላል" ብለዋል አቶ ከድር።

ይህም ሆኖ ግን እስካሁን የገቢ ግብር ቅነሳውም ቢሆን ተግባራዊ አለመደረጉን ጠቁመዋል።

ቢቢሲ በመጨረሻም ለባለሙያዎቹ ምላሽ ካላገኛችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል? በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ የሚከተለውን መልሰዋል።

"ሥራ ለማቆም አላሰብንም። ባለሙያው ሥራ እንዳያቆም ነው ተወካይ የተላከው። ተወካዮች ኮሚቴ መረጡ። እነሱ ናቸው የሚንቀሳቀሱት። ኮሚቴዎቹ ሥራም እየሠሩ ነው። በሚዲያ እያሳወቅን ነው ህዝቡ እንዲያውቅልን። በኮሚቴም በአባላትም ደረጃ ወደፊት ወደ ፍርድ ቤት ልናመራ እንችላለን የሚል ሃሳብ ነው ያለው" ያሉት አቶ ዲኖ ናቸው።

"አገራዊ እና ሙያዊ ግዴታ ነው። እኔ ሥራ ባቆም የሚሞቱ ሰዎች አሉ። ይሄ ባለሙያው ምሎ የወጣበት ስለሆነ ሥራ ማቆም አይችልም። አመጽም አይኖርም። እየተረገጥክ ጥቅመህን አሳልፈን እንድትኖር ነው የሚያደርጉት" ያሉት ደግሞ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሐኪም ናቸው።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምላሽ

ዶ/ር ሙሉጌታ እንዳለ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናቸው።

እንደ ዶ/ር ሙሉጌታ ከሆነ ልዩ አበሉን ለማስፈጸም መመሪያ ከወጣ በኋላ አፈጻጸም ላይ ችግር ገጥሟቸዋል።

በመጀመሪያው የልዩ አበሉ የተፈቀደው የኮቪድ -19 ማዕከላት ውስጥ ለሚሠሩ እና በመከላከል ላይ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች በሚል ነው።

እንደ ምክትል ኃላፊው ከሆነ ግን በዚህ ውስጥ ሁሉም የጤና ሠራተኞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየተሳተፉ ነበር አሁንም በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ምክንያት ለማስፈጸም አስቸግሮናል ይላሉ።

በተጨማሪም ደግሞ ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች በራሳቸው አውድ እንዲጠቀሙበት መመሪያው እንደሚፈቅድ ገልጸው የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ ለመተግበር ሙከራ መደረጉን አስታውቀዋል።

ሆኖም ሙከራዎቹ ጥቂት ሠራተኞችን ብቻ የሚጠቅሙ ሆነው ተገኝተዋል ይላሉ።

"መሬት ላይ ስናወርደው ጽዳቱም፣ ሹፌሩም ድንገተኛ ክፍል የሚሠራው ይገባዋል። ተመላላሽ ህክምና፣ ቀዶ ጥገና ክፍል፣ ማዋለጃ የሚሠሩና ሁሉም ላይ ያሉ ሠራተኞቻችን ከኮቪድ -19 ጋር ተጋፍጠው እየተከላከሉ እየሠሩ ነው። እንተግብረው ካልን ደግሞ ለሁሉም ነው መተግበር ያለብን" ሲሉ ያስረዳሉ።

ሌላው ደግሞ ለትግበራ ያስቸገረው የበጀት ጥያቄ ነው። "የከተማ አስተዳድሩ ላይ ትልቅ ወጪ አለ። ከተማ አስተዳደሩ ያንን መሸከም የሚችል አይደለም" ብለዋል።

ከዚህ በተሻለ አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ ከገባበት ወቅት አንስቶ በከተማ መስተዳድሩ በጤና ዘርፍ ለሚሠሩ ባለሙያዎች በሙሉ የግብር ቅነሳ ማድረግ ነው።

"ሁሉም የጤና ዘርፍ ሰራተኞች ራሳቸውም አደጋ ላይ ጥለው ነው እየሠሩ ያሉት። ኮቪድ-19 ላይ ቅዳሜ እና እሁድ ገብተው የሚሠሩ አሉ። ገብተው የሚያድሩ አሉ። ይሄንን የትርፍ ሰዓት ክፍያቸውን እንሰጣለን" ሲሉ ተናግረዋል ።

አክለውም "ከተማ መስተዳድሩ ታክስ ቅነሳ ወይም ራሱ መስተዳድሩ ታክሱን ይከፍላል ማለት ነው። ስለዚህ ኮቪድ-19 ከጀመረበት ከመጋቢት ጀምሮ ኮቪድ-19 ከስጋትነት እስከሚወጣበት ድረስ ሁሉም የጤና ሠራተኞቻችን ያንን ከግብር ተቀንሶላቸው መስተዳድሩ ራሱ እየሸፈነ በዚያ መንገድ እናስተናግድ ተብሎ ተወሰነ" ብለዋል።

መመሪያው ሲወጣ መጀመሪያ ድንገተኛ የአደጋ መቆጣጠር ዘርፍ ላይ የሚሠሩ የተወሰኑ ሠራተኞችን ብቻ ታሳቢ አድርጎ እንደነበር ዶ/ር ሙሉጌታ አስታውቀው፤ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ሲሄድ ብዙ ባለሙያዎችን ከማሳተፉም በላይ መመሪያዎችም መቀያየራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኮሮናቫይረስ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች ቁጥር መጨመርም ሌላው ምክንያት ነው።

ቸግሩን ለመቅረፍ ከሠራተኞች ጋር በተደጋጋሚ መወያየታቸውን አንስተው "ብዙ የጤናው ዘርፍ ሠራተኛ በውሳኔው ላይ ጥሩ እይታ እንዳለው ነው ያየነው" ብለዋል።

ሆኖም ቅሬታዎች መኖራቸውን ጠቁመው ጤና ቢሮው የወሰደውን እርምጃ ሌሎችም (ክልሎች እና ጤና ጥበቃ) የመከተል ነገር እንዳለ መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ሁላችንም ለአደጋ ተጋልጠን በምንሠራበት ለጥቂቶች ብቻ መከፈል የለበትም የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸውን በተመለከተ፤ "እኛም አደጋ ላይ ወድቀን እየሠራን ለጥቂቶች ብቻ እየተከፈለ ታሳቢ አለመደረጉ ተገቢ አይደለም ብለው ደግሞ በተቃራኒው የሚጠይቁ አሉ። የግድ ኮቪድ-19 ማከሚያ ቦታ ብቻ ነው ወይ እኛም እየተጋፈጥን ነው የሚሉ አሉ" ሲሉ አስረድተዋል።

ገቢ ግብርን በተመለከተ ደግሞ በከተማ መስተዳድሩ ሥር በሚገኙ ሁሉም ጤና ተቋማት መረጃ የማሰባሰብ ሥራ መከናወኑን አስታውቀው በጥቂት ቀናት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

ህክምና ባለሙያዎቹ ቤት ይሰጣችኋል ተብለን በተገባልን ቃል መሠረት አልተፈጸመልንም ለሚለው ቅሬታቸውም ምላሻውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል።

"ቤት ይሰጣል የሚል እንደ መስተዳደርም እንደ ቢሮም የለም። መረጃ ሊሰበሰብ ቤት ያለውን እና የሌለው የጤና ባለሙያ መረጃ እንዲያዝ ከተማ መስተዳደሩ መጠየቁን ነው እኔ የማውቀው። መረጃውን ጠይቁ አለ መረጃውን ሰብስበን ልከናል። ቤት ይሰጣቸዋል የሚል ነገር ግን የለም" ብለዋል።