140 ስደተኞች ሴኔጋል አቅራቢያ ሰጥመው ሞቱ

ታትሟል

የተባበሩት መንግሥታት ወደ 200 የሚጠጉ ስደተኞችን ጭና ወደ አውሮፓ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሴኔጋል አቅራቢያ ሰጥማ 140 ስደተኞች መሞታቸውን አስታወቀ።

ጀልባዋ ማቡር ከምትባለው የሴኔጋል ከተማ ከተነሳች በኋላ በእሳት ተያይዛ መስጠሟን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አረጋግጧል።

አደጋው የደረሳው ባለፈው ቅዳሜ ነበር።

ከአደጋው 60 ሰዎች በሕይወት መትረፍ መቻላቸው ተጠቁሟል።

ስደተኞቹ የስፔን ካናሪ ደሴትን በማቋረጥ መዳረሻቸውን አውሮፓ ለማድረግ የተነሱ ነበሩ ተብሏል።

ከእአአ 2018 ጀምሮ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ስደተኞች አውሮፓ ለመድረስ ይህን አቅጣጫ አዘውትረው ይጠቀሙበታል።

የተባበሩት መንግሥታት ይህ አደጋ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል በስደተኞች ላይ ከደረሱት አደጋዎች አስከፊው ነው ብሏል።

በሴኔጋል የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ተወካይ ባካይ ዱምቢዓ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ለማጥፋት አገራት እና ድርጅቶች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የስፔን መንግሥት በዚህ ዓመት ብቻ 11ሺህ ስተደኞች በካናሪ ደሴት መመዝገባቸውን አስታውቋል።

ይህ አሃዝ ከአንድ ዓመት 2ሺህ500 ገደማ እንደነበረ የስፔን መንግሥት ጨምሮ አስታውቋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በበኩሉ እስካሁን በዚህ አቅጣጫ አውሮፓ ለመድረስ በሚደረግ ጥረት ቢያንስ 414 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።