ፓራጓይ ኮንቴይነር ውስጥ የሰባት ስደተኞችን አስክሬን አገኘች

ታትሟል

የፓራጓይ ባላስልጣናት ኮንቴይነር ውስጥ የሰባት የስደተኞች አስክሬን የአገሪቱ ፖሊስ ማግኘቱን አስታወቁ።

የሰደተኞቹ አስክሬን በኮንቴነር ውሰጥ ለረዥም ጊዜ መቆየቱን ተከትሎ አስክሬናቸው መበስበሱ ተጠቁሟል።

የእርሻ ማዳበሪያ ኮንቴይነሩ ሰኔ ወር ላይ ከአውሮፓዊቷ አገር ሰርቢያ የተነሳ እንደሆነም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

ስደተኞቹን የጫነው ኮንቴይነር ከሰርቢያ በክሮሺያ አድርጎ በግብጽ፣ ስፔን እና አርጀንቲና በኩል አድርጎ ፓራጓይ ደርሷል። ሰደተኞቹ መዳረሻቸውን ክሮሺያ ለማድረግ አስበው ኮንቴነር ውስጥ ሳይሳፈሩ እንዳልቀረ ተገምቷል።

አስክሬናቸው ከተገኘው ስደተኞች መካከል ሰባቱ ሶስቱ ከሞሮረኮ ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ከግብጽ እንደሆነ የአስክሬን ምርመራ ባለሙያው ፓብሎ ሌሚር ገልጸዋል።

የስደተኞቹን አስክሬን የያዘው ኮንቴይነር የተገኘው በዋና ከተማዋ አሱንሲዮን ሲሆን፤ አስክሬኑን ያገኙት ደግሞ በአንድ የግብርና ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ድርጅት ሰራተኞች ናቸው።

ለስደተኞቹ ሕይወት ማለፍ የአየር እጥረት ሳይሆን እንዳልቀረ የተገመተ ሲሆን ሁሉም ሟቾች አዋቂ ወንዶች ናቸው።

በኮንቴይነሩ ውስጥ የነበረው ማዳበሪያም የሟቾቹን አስክሬን እንዲበሰብስ እንዳደረገው የአስክሬን ምርመራ ባለሙያው ፓብሎ ሌሚር ገልጸዋል። ከስደተኞቹ አስክሬን በተጨማሪ በሰርቢያዊ የተቆረተ የታክሲ ደረሰኝ የተገኘ ሲሆን የስልክ ካርድና አንዳንድ ምግቦችም አብረው ተገኝተዋል።

''በእኛ ግምት ስደተኞቹ በመጀመሪያ ሰርቢያ ከደረሱ በኋላ ቅርብ ወደሆነው የአውሮፓ አገር ለመግባት ጥረት ሳያደርጉ አልቀሩም። ነገር ግን ከመነሻ እስከ መድረሻ ያለውን ጊዜ በትክከል ያሰቡበት አይመስለንም። ለዚህም ነው ታፍነው ሕይወታቸው ሊያልፍ የቻለው'' ብለዋል አቃቤ ሕጉ ማርሴሎ ሳልዲቫር ከሬውተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

አክለውም የሰዎቹ አስክሬን ከሶስት ወራት በላይ በመቆየቱ የበሰበሰ ሲሆን መገኘት የቻለው ቅሪተ አካል ጸጉርና አጥንት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሟቾቹን ትክክለኛ ማንንት ለማጣራትም ምርመራ እየተካሄደ ነው።