አሜሪካ፡ ኤፍቢአይ ኢራንና ሩሲያ የአሜሪካ መራጮች መረጃ አላቸው አለ

ታትሟል

የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ባስልጣናት ለዴሞክራቲክ መራጮች እየተላኩ ላሉት የማስፈራሪያ መልእክት (ኢሜይል) ኢራን ተጠያቂ መሆኗን አስታውቀዋል።

የተላኩት ኢሜይሎች ከቀኝ ዘመም የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች እንደሆኑ በማስመሰልና በአገሪቱ አለመረጋጋትን ለመፍጠር ታልመው የተዘጋጁ እንደሆነ የብሄራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩ ጆን ራትክሊፍ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም የአሜሪካ ባለስልጣነት ኢራንና ሩሲያ የመራጮች መረጃ እንዳላቸው ደርሰውበታል ሲሉ ተደምጠዋል።

እንዲህ አይነት መረጃ የወጣው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 13 ቀናት ሲቀሩት ነው።

ምርጫው እንዲህ ተቃርቦ ባለበት በዚህ ወቅት ባልተለመደ መልኩ የደህንነት ቢሮው እንደዚህ አይነት መረጃ ይፋ ማድረጉ ደግሞ መንግሥት ከምርጫው ጋር በተያያዘ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርና የተሳሳተ መረጃ እንዳይሰራጭ ስጋት እንዳለበት ማሳያ ነው ተብሏል።

'' ከኢራን የመነጩት አሳሳች መልእክቶች (ኢሜይሎች) መራጮችን ለማስፈራራትና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ጉዳት ለማድረስ የታለሙ ናቸው'' ብለዋል ዳይሬክተሩ።

አክለውም የመራጮች የግል መረጃን በመጠቀም ሐሰተኛ መረጃን በማሰራጭና መራጮችን ግራ በማጋባት በአሜሪካ ያለውን ዴሞክራሲ ለማንቋሸሽ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም የደህንነት ባለስልጣናት ''ተመሳሳይ መልዕክቶችን ከሩሲያ በኩል አለማግኘታቸውንና የመራጮች መረጃ ግን አሁንም በሩሲያ እጅ እንዳለ'' ገልጸዋል።

በበርካታ ግዛቶች የመራጮች መረጃ በይፋዊ ጥያቄ መገኘት የሚችል ሲሆን በእያንዳንዱ ግዛት ግን የሚያስፈልጉ መስፈርቶች የተለያዩ ናቸው።

''የሚያስፈራሩና ነገሮችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመምራት የሚያልሙ መልዕክቶች (ኢሜይሎች) ከደረሷችሁ አትደናገጡ፤ ለሌሎችም አታጋሩ'' ብለዋል የብሄራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩ ጆን ራትክሊፍ።

የአሜሪካ ፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ዳይሬክተሩ ክሪስቶፈር ሬይ በበኩላቸው የደህንነት ኃላፊውን ሀሳብ ደግፈዋል።

''ሁላችሁም ልታውቁት የሚገባው፤ የሁላችሁም ድምጽ ይቆጠራል፤ ያልተረጋገጡና ቀድመው የምርጫውን ውጤት የሚተነብዩ መረጃዎችን በጥርጣሬ መመልከት አለባችሁ'' ሲሉም ተደምጠዋል።

ሁለቱም ባለስልጣናት ኢራንና ሩሲያ መረጃውን ከየትና እንዴት እንዳገኙት አልያም መረጃውን ለምን ጥቅም ላይ እንደሚያውሉት የሰጡት ምንም ተጨማሪ ማብራሪያ የለም።