ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአውስትራሊያ አረጋውያን እንክብካቤ ማዕከላት በየሳምንቱ 50 ወሲባዊ ጥቃቶች ይደርሳሉ ተባለ
በአውስትራሊያ የሚገኙ የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ በየሳምንቱ አምሳ ያህል ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚደርሱ ከሰሞኑ ብሔራዊ አጣሪ ኮሚቴ ይፋ አድርጓል።
ለሁለት አመታት ያህልም በአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከላት የሚደርሱ የተለያዩ ጥቃቶችንና መንገላቶችን ይፋ ባደረገበት መረጃ ነው ሮያል ኮሚሽን ይህንንም ያካተተው።
መርማሪዎቹ እንዳሉት በጎሮጎሳውያኑ 2018-2019 ጊዜ 2 ሺህ 520 አረጋውያን ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
"ይህ ሁኔታ ብሔራዊ እፍረት ነው" ብለውታል የምክር ቤት አባሉ ፒተር ሮዝን ኪው ሲ ለአጣሪው ኮሚቴ
"ቁጥሮቹ የሚረብሹትን ያህል እነዚህን መረጃዎች ያገኘው የመንግሥት አካል ክትትትልና ቁጥጥር አለማድረጉ የበለጠ የከፋ ነው" ብለዋል።
በአረጋውያኑ የእንክብካቤ ማዕከል ላይ የሚታየው ቸልተኝነት ከፍተኛ ውዝግብና ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን ከዚህ ቀደምም በአውስትራሊያ በኮሮናቫይረስ ከሞቱት አብዛኛዎቹ በአረጋውያን ማዕከል የሚገኙ ናቸው።
አውስትራሊያ በኮሮናቫይረስ ሞተዋል ብላ ከመዘገበችው 903 ሰዎች መካከል 75 በመቶ በነዚህ ማዕከላት የሚገኙ ናቸው።
በእነዚህ ማዕከላት ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶች የቀደመ ስጋት ሆነው የቆዩ መሆናቸውን ያመኑት ፒተር ሮዝን ቁጥሩም በአገሪቱ ያሉትን 13-18 በመቶ ጥቃት እንደደረሰባቸው ያሳያል።
በርካቶች በዕድሜያቸው የበለፀጉ ወይም ተጋላጭ የሆኑ ቤተሰቦቻቸውን በአረጋውያኑ ማዕከል የሚያስገቡት ደህንነታቸው ይጠበቃል በሚል ዕምነትም እንደሆነም የምክር ቤት አባሉ አስረድተዋል።
"በአረጋውያን ማዕከላት የሚገኙ ሰዎች ከማህበረሰቡ በበለጠ ለወሲባዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸው ተቀባይነት የለውም" ብለዋል ፒተር ሮዝን
በአጠቃላይ መርማሪዎች እንደሚገምቱት 32 ሺህ ያህል ወሲባዊ፣ አካላዊና የስነልቦናዊ ጥቃቶች መድረሳቸውን ነው። ይህም ቁጥር በአንድ አመት ያህል እንደደረሰ መረጃው ጠቁሟል።
ወሲባዊ ጥቃቱ እንክብካቤ በሚሰጡ ግለሰቦች እንዲሁም እዛው ባሉ ነዋሪዎች እንደሚፈፀምም መረጃው ይፋ አድርጓል።